“ምርጫ ፉክክር ቢኖረውም ለሰላማዊነቱ በትብብር አብሮ መሥራት ይገባል” ብልጽግና ፓርቲ

210
“ምርጫ ፉክክር ቢኖረውም ለሰላማዊነቱ በትብብር አብሮ መሥራት ይገባል” ብልጽግና ፓርቲ
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 05/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ብልጽግና ፓርቲ በምዕራብ ጎጃም ዞን ፍኖተ ሰላም ከተማ ከአባላቱ እና ከደጋፊዎቹ ጋር የፕሮግራም ትውውቅና ውይይት አካሂዷል።
ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ የብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ብናልፍ አንዷለም አስገንዝበዋል። 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሀሳባቸውን በነፃነት የሚያቀርቡበት፣ ሕዝቦች በነፃነት የፈለጉትን መምረጥ የሚችሉበት ሥርዓት መሆን እንደሚገባውም አንስተዋል።
ብልጽግና ዴሞክራሲን በኢትዮጵያ በተግባር ማሥፈን ዋነኛ ግብ አድርጎ እየሠራ እንደሚገኝም ገልጸዋል። ይህንን ለማድረግ በዞኑ የሚወዳደሩ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም በሰላማዊ እና በሰለጠነ መንገድ ሀሳባቸውን መግለጽ፣ አማራጮቻቸውን ማቅረብ እና በመጨረሻ ሕዝቡ የሚሠጣቸውን ድምጽ በጸጋ መቀበል ይገባቸዋል ብለዋል።
“ምርጫ ፉክክር ቢኖረውም ለሰላማዊነቱ በትብብር አብሮ መሥራት ይገባል” ብለዋል አቶ ብናልፍ። ብልጽግና በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት መንግሥት ሆኖ ለመቀጠል የሚያስችለውን ድምጽ ለማግኘት ማኒፌስቶውን የማስተዋወቅ ሥራ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብርሃም አለኸኝ እንዳሉት ብልጽግና ለአምሳ ዓመታት የሕዝቦችን አንድነት ለማፈራረስ ሲሰሩ የቆዩ ቡድኖችን በማሸነፍ ለሁሉም እኩል የሆነች ዴሞክራሲያዊት ሀገር ለመገንባት እየሠራ ይገኛል።
ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ማኅበረሰቡ የአካባቢውን ሰላም እንዲጠብቅም አሳስበዋል።
በፕሮግራም ትውውቁ የገቢዎች ሚኒስትር ላቀ አያሌው፣ የምዕራብ ጎጃም ዞን አስተዳዳሪ ስሜነህ አያሌው እና ሌሎች የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፣ በመርሃ ግብሩ የተወዳዳሪ ዕጩዎች ትውውቅም ተደርጓል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ኾኖ እንዲጠናቀቅ ንቁ ተሳትፎ እያደረጉ መኾናቸውን በደቡብ ጎንደር ዞን የስማዳ ወረዳ የብልጽግና ፓርቲ ደጋፊዎች ተናገሩ፡፡
Next articleበድጋሜ የወጣ የዜና ወኪል ቅጥር ማስታወቂያ