ታሪኳን የማይመጥን የቆሻሻ አወጋገድ ችግር የገጠማት ከተማ።

297

ታሪኳን የማይመጥን የቆሻሻ አወጋገድ ችግር የገጠማት ከተማ።
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 06/2013 ዓ.ም (አብመድ) መንግሥት ዜጎች ንጹህና ጤናማ በሆነ አካባቢ እንዲኖሩ የማድረግ ኃላፊነት
እንዳለበት በኢፌዴሪ ሕገመንግሥት ንዑስ አንቀጽ አንድ ላይ ተቀምጧል። በንዑስ አንቀጽ አራት ላይ ደግሞ መንግሥት እና ዜጎች
የአካባቢያቸውን ንጽህና የመጠበቅ ግዴታ እንዳለባቸው አስቀምጧል።
ይሁን እንጅ የቆሻሻ አወጋገድ ችግር ለሰዎች ጤንነት እና ለአካባቢ ብክለት ስጋት እየሆነ መጥቷል። በተለይም በከተሞች ያለው
የቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ትኩረት ተነፍጎታል። የደብረታቦር ከተማም የችግሩ ሰለባ ከሆኑት ከተሞች አንዷ ናት። የከተማዋ የቆሻሻ
አሰባሰብም ሆነ አወጋገድ ሥርዓቱ ኋላቀር በመሆኑ ከተማዋ ጸድታ አትታይም፡፡
በከተማዋ ከየቤቱ የሚወጣው ደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻ እስከ ዋና ማስወገጃው ድረስ ማስቀመጫ ቦታ ባለመኖሩ በከተማዋ የተለያዩ
ቦታዎች ተበትኖ ይገኛል። የቆሻሻ አያያዝ ስርዓቱ ለጤናቸው ጠንቅ እየሆነ በመምጣቱ መፍትሔ እንዲያገኙ በተለያየ ጊዜ
ቢጠይቁም የሚሰማ ጆሮ አለማግኘታቸውን የከተማዋ ነዋሪዎች ተናግረዋል። ኅብረተሰቡም ሆነ የቆሻሻ አወጋገዱን በበላይነት
የሚመራው የከተማዋ አስተዳደር ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት በኩል ክፍተት እንዳለ ገልጸዋል።
ከከተማዋ ነዋሪዎች መካከል የህብረት ሆቴል ሥራ አስኪያጅ ጌታነህ ውዱ እንዳሉት በሆቴላቸው እስከ አምሳ ሜትር አካባቢ
ቆሻሻን የማጽዳት ሥራ እያከናወኑ እንደነበር ነግረውናል። ይሁን እንጅ በተጸዳው ቦታ በሌሊት ቆሻሻ ተከማችቶ ስለሚያገኙት
በመሠላቸት እንደተውት ገልጸዋል። የቆሻሻ አወጋገድ ለአንድ ድርጅት ወይንም ለተወሰነ የህብረተሰብ ክፍል የሚተው ሳይሆን
የከተማውን ነዋሪዎች የባለቤትነት ስሜት የሚጠይቅ እንደሆነም አንስተዋል። የከተማ አስተዳደሩም በቆሻሻ አወጋገድ ዙሪያ
ለማሕበረሰቡ ግንዛቤ መፍጠር፣ የቆሻሻ ማስወገጃ የማዘጋጀት እና የመከታተል ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት ተናግረዋል።
ሌላኛው ሀሳብ ሰጭ አቶ ሞላ አለኸኝሰው ደብረታቦር ከተማ በጥሩ እድገት ላይ ብትገኝም የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓቱ የተዝረከረከ
፣ ለማሕበረሰቡም የጤና ጠንቅ እየሆነ መምጣቱን አንስተዋል። አስተያየት ሰጭው እንዳሉት የአገልግሎት መስጫ ተቋማት በቂ
ማስወገጃ የላቸውም፤ ከውጭ የተከማቸ ቆሻሻን በፍጥነት የማንሳት ችግር ይታያል። የተደራጁ ማሕበራትም በተገቢው መንገድ
ሲያስወግዱ አይታይም። ከተማ አስተዳደሩም ማኅበራቱን አንቀሳቅሶ በማሠራት በኩል ችግር እንዳለ አንስተዋል።
በደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ቤቶች ልማት ኮንስትራክሽን አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ጽዳት እና ውበት አረንጓዴ ልማት ቡድን መሪ
ግዛቸው ካሳ ከከተማዋ የህዝብ ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ የደረቅ እና ፈሳሽ ቆሻሻ አሰባሰብ እና አወጋገድ ችግር ማጋጠሙን
ነግረውናል።
የከተማዋን የ2006 ዓ.ም ጥናት መሠረት አድርገው እንደነገሩን በከተማዋ በቀን ከሚመነጨው ቆሻሻ የሚወገደው 27 በመቶው
ብቻ ነው። ቀሪው ቆሻሻ ደግሞ በአካባቢው ተበተኖ እንደሚቀር ነው ቡድን መሪው የገለጹት። በከተማ አስተዳደሩ ስድስቱ
ቀበሌዎች በትንሹ ስድስት ማሕበራት ቢያስፈልጉም አንድ ሀምሳ አባላት ያለው የደረቅ ቆሻሻ አንሽ ማሕበር ብቻ ነው የማሰባሰብ
እና ማስወገድ ሥራውን እያከናወነ የሚገኘው።
ማሕበሩ የከተማውን ቆሻሻ የሚያስወግደው በሁለት ጋሪዎች ብቻ ነው። በዚህም ምክንያት የከተማዋ የደረቅ እና ፍሳሽ ቆሻሻ
በተለይም ደግሞ የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ የከተማዋ ሥጋት ሆኗል፤ በከተማዋ ገጽታ ላይም ተጽዕኖ አሳድሯል ብለዋል። የቆሻሻ
አሰባሰብ ብቻ ሳይሆን ቆሻሻ የሚወገድበት ዋናው ቦታም ደረጃውን የጠበቀ አደለም ነው ያሉት።
አቶ ግዛቸው እንዳሉት የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ ቦታው በፕላን የተመላከተና ደረጃውን የጠበቀ ሳይሆን በጊዜያዊነት የተዘጋጀ
ነው። በዚህም ምክንያት በክረምት ወቅት ከጎርፍ ጋር ተቀላቅሎ ወደ ውጭ በመፍሰስ የአካባቢ ብክለት እና በማሕበረሰብ
ጤንነት ላይ ችግር ከመፈጠሩ በፊት መፍትሄ ማግኘት እንደሚገባው ለሚመለከተታቸው የሥራ ኃላፊዎች ማቅረባቸውን
ነግረውናል። እስከ አሁንም መፍትሄ አለማግኘቱን አንስተዋል። የአመራሩ እና የሕብረተሰቡ በቆሻሻ አሰባሰብ እና አወጋገድ ላይ
ያለው አመለካከት አለመለወጥ፣ አገልግሎት ጽሕፈት ቤቱ እስከቀበሌ የተዘረጋ አደረጃጀት አለመኖሩ በችግርነት መቀመጣቸውን
ገልጸዋል።
የአሰባሰብ እና የአወጋገድ ሥርዓቱን የሚሰሩ አጋር አካላት ቅንጅታዊ አሰራር ችግር መኖሩንም አንስተዋል። የተሟላ ግብዓት
አለመኖር፣ ማሕበረሰቡ የሚጠየቀውን ክፍያ አለመክፈል እና መንግሥትም የሚጠበቅበትን ድጋፍ አለማድረግ ለቆሻሻ አወጋገድ
ስርዓቱ ችግሮች መሆናቸውን አንስተዋል።
ቆሻሻን ለማስወገድ የሚያጋጥመውን የገንዘብ ችግር ለመቅረፍ ነዋሪዎች ከውኃ ቆጣሪ ጋር መክፈል የሚያስችል መመሪያ
በከተማ አስተዳደር ምክር ቤት መጽደቁንም ገልጸዋል።
የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ወንዴ መሠረት ማሕበረሰቡ የሰበሰበውን ቆሻሻ ከቅጥር ግቢው
ማስቀመጥ ሲገባ በስውር በመንገድ አካፋይ ጭምር ማስቀመጥን እየተላመደ መምጣቱን ገልጸዋል። አቶ ወንዴ እንዳሉት
የቆሻሻ አወጋገዱን ችግር ለመቅረፍ እያንዳንዱ ግለሰብ በግቢው 20 ሜትር ራዲየስ ላይ የሚገኘውን ቆሻሻ እንዲያስወግድ
ሥምምነት ላይ ቢደረስም ችግሩን መፍታት አልተቻለም። በዚህም ምክንያት ከከተማዋ የሚመነጨው ቆሻሻ ከከተማ አስተዳደሩ
አቅም በላይ መሆኑን ገልጸዋል። ከተማ አስተዳደሩ ባጋጠመው የበጀት ችግር ቆሻሻን ማስወገድ አልቻለም።
ይሁን እንጅ ከተማ አስተዳደሩ በከተማ ሴፍትኔት ፕሮግራም በመታቀፉ ችግሩ እንደሚቃለል አንስተዋል።
የአብመድ የጋዜጠኞች ቡድንም የከተማዋን ዋናው አካፋይ መንገድ ጨምሮ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች፣ የገበያ ቦታዎች ቆሻሻ
ተከማችቶባቸው ተመልክቷል። ቦዮች ለውኃ መፋሰሻ ሳይሆን ለቆሻሻ ማከማቻ የተሰሩ ይመሥላሉ። አንዳንዶቹም ሙሉ በሙሉ
በደረቅ ቆሻሻ ተዘግተዋል። ዋናው የቆሻሻ ማስወገጃ ቦታም አስፋልት ዳር በመሆኑ እንስሳት የወዳደቁ ፕላስቲኮችን ሲመገቡ፣
ሰዎችም መንገድ አድርገውት አስታውለናል። የችግሩ ስፋትም ትኩረትን ይሻል፡፡
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleየዜና ወኪል ቅጥር ማስታወቂያ
Next articleʺምድር ብትጨነቅ ሠማይ ቢሰነጠቅ ፣ መች ይሸበርና የምሥራቁ መብረቅ”