“የሕዝቦችን አንድነት የሸረሸረውን የህወሃት የተሳሳተ ትርክት ለማጽዳት እየተሰራ ነው” የክልል ምክር ቤቶች

188
“የሕዝቦችን አንድነት የሸረሸረውን የህወሃት የተሳሳተ ትርክት ለማጽዳት እየተሰራ ነው” የክልል ምክር ቤቶች
ባሕር ዳር፡ ጥር 25/2013 ዓ.ም (አብመድ) የኢትዮጵያዊያንን አንድነት የሸረሸረውን የህወሃት የሃሰት ትርክት ከመሰረቱ ለማስወገድ እየተሰራ መሆኑን የክልል ምክር ቤቶች አፈ ጉባዔዎች ገለፁ።
የአማራ፣ የቤኒሻንጉል ጉምዝና የደቡብ ክልሎች ምክር ቤቶች አፈ ጉባዔዎችና የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እንደገለጹት፤ በየአካባቢያቸው የሕዝቦችን አንድነትና ትስስር የሚያጠናክሩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።
የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ወይዘሮ ወርቅሰሙ ማሞ “በአገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች በዜጎች ላይ የሚፈፀም ግድያ፣ ማፈናቀልና ንብረት ማውደም የኢትዮጵያዊያን መገለጫዎች አይደሉም” ብለዋል። እነዚህ ተግባራት የህወሃት አመራሮች የሴራ ፖለቲካ ስልት የሆነው ሕዝብን በመከፋፈል የግል ጥቅም ማሟያዎች መሆናቸውን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያዊያን አገራቸውን በጋራ ከማልማት ይልቅ እርስ በርስ በመጋጨት ለልማት፣ ለሠላምና ለአንድነት ትኩረት እንዳይሰጡ ሲሰራ እንደነበር አስታውሰዋል።
“የሕዝቦች ጠላት የሆነው ህወሃት በትብብር ይደምሰስ እንጂ ፍርስራሾቹ ኦነግ ሸኔና በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች በመኖራቸው እነዚህን ከመሰረቱ ለማፅዳት አሁንም ትኩረት ያሻል” ብለዋል።
በመሆኑም የአማራ ክልል ምክር ቤት በህወሃት አመራሮች የተሳሳተ ትርክት የተሸረሸረውን የሕዝቦች አንድነት ለመመለስ በተለየ ሁኔታ እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።
“የሕዝቦችን አንድነት፣ ወንድማማችነትና እህትማማችነት መልሶ ማጠናከር የሚያስችሉ ኮንፍረንስና ሌሎች ሁነቶች ከወትሮው በተለየ ይሰራባቸዋል” ብለዋል ወይዘሮ ወርቅሰሙ።
የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ታደለ ተረፈ በበኩላቸው ባለፉት 28 ዓመታት ሀገራዊ አንድነት እንዲቀጭጭና የብሔር ማንነት ጎልቶ እንዲወጣ መሰራቱ ትልቅ ችግር መሆኑን አውስተዋል።
“በዚህም ዜጎች ከሚኖሩበት አካባቢ ተፈናቅለዋል፣ ተገድለዋል ለዘመናት ያፈሩትን ንብረትም አጥተዋል” ብለዋል።
ችግሩን ለመፍታት ክልሉ ከሚያዋስናቸው አማራና ኦሮሚያ ክልሎች ጋር የቀደመ አብሮነቱን ለመመለስ ልማትና ማኅበራዊ ግንኙነቶችን የሚያጠናክሩ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።
አቶ ታደለ የብሔር ማንነትና አገራዊ አንድነት ሚዛናቸውን ጠብቀው እንዲሄዱ ጠንካራ ስራ እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል።
“በደቡብ ክልል የሕዝቦችን አንድነት ለማጠናከርና መቻቻልን ለማጎልበት እየተሰራ ነው” ያሉት በክልሉ ምክር ቤት የግብርናና ገጠር ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ቀለምወርቅ ለገሰ፤ የሚከሰቱ ችግሮችን ከመሰረታቸው ለመፍታት እየተሰራ እንደሆነ ገልጸዋል። የዘገበው ኢዜአ ነው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleየሴቶችን ውሳኔ ሰጭነት እና አመራርነት ሚና ማሳደግ የሁሉም ድርሻ መሆኑን ሴት የሥራ ኀላፊዎች ገልጹ፡፡
Next articleየቡሬ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታው ተጠናቅቆ ጥር 30/2013 ዓ.ም ሊመረቅ ነው፡፡