ጣና ሐይቅንና የአረንጓዴ ልምትን ቀዳሚ ተግባሩ ያደረገው ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎቹን ለማስመረቅ ተዘጋጅቷል።
ባሕር ዳር ፡ ጥር 21/2013 ዓ.ም (አብመድ)
በ2001 ዓ.ም የመሠረት ድንጋይ ተቀምጦለት ከሦስት ዓመታት በኋላ ወደ ተግባር የገባው የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ከሦስተኛ ትውልድ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ አንዱ ነው።
የዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ የኢንዱስትሪ ጥማት ተጸንሶ በተወለደበት የጋፋት ኢንዱስትሪ መንደር አቅራቢያ የተመሠረተው ዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር ሥራውን የጀመረው በ2004 ዓ.ም 623 ተማሪዎችን በመቀበል ነበር፡፡
ዩኒቨርሲቲው ባለፉት ዓመታት በመደበኛ በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ እንዲሁም በክረምትና ኤክስቴንሽን የትምሕረት መርሃ ግብሮች 14 ሺህ 437 ተማሪዎችን አስመርቋል፡፡ ከነዚህ ውስጥም 5 ሺህ 7 ሴቶች ነበሩ።
በተከታታይ የትምህርት መርሃ ግብርም እስካሁን 3 ሺህ 249 ተማሪዎችን አስመርቋል።
ዩኒቨርሲቲው በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜም 39 የሜዲካል ዶክተር ተማሪዎችን ያስመረቀው ባለፈው ዓመት ነበር፡፡
በ2012 ዓ.ም 15 ሺህ ተማሪዎችን በመደበኛና 6 ሺህ 161 ተማሪዎችን ደግም በተከታታይ ትምህርት መርሃ ግብሮች ሲያስተምር መቆየቱን
የዩኒቨርሲቲው የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ዳዊት ብርሃኑ በተለይ ለአብመድ ተናግረዋል፡፡
ዩኒቨርስቲው በ2013 ዓ.ም በመደበኛው መርሃ ግብር በመጀመሪያ ዲግሪ 1 ሺህ 905 እና በሁለተኛ ዲግሪ 32 ተማሪዎችን በኤክስቴንሽን ደግም 581 ተማሪዎችን ለማስመረቅ በዝግጅት ላይ መሆኑንም አቶ ዳዊት ገልጸዋል።
ከተመራቂዎች 1ሺህ 8 ሴቶች መሆናቸውም ታውቋል።
አቶ ዳዊት እንዳሉት የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ በእንቦጭ አረም ማስወገድ፣ በተፈጥሮ ሀብት ልማትና አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ በሚያደርጉ ምርምሮች ላይ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል፡፡
ዩኒቨርሲቲው የጣና ሐይቅን ከእምቦጭ አረም ለመታደግ በጣና ዙርያ በሚገኙ አራት ቀበሌዎች በሁለት ዙር (በ52 ቀናት ውስጥ) 47 ሔክታር መሬት ላይ እምቦጭን የማስወገድ ሥራዎችን አከናውኗል ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፡፡
በዚህ ዓመትም ጥቅምት ላይ የዩኒቨርሲቲው በጎ ፍቃደኛ መምህራንና ሠራተኞች በጋራ በመሆን የዓመቱን የመጀመሪያ ዙር የእምቦጭ ማስወገድ ዘመቻ አከናውነዋል ብለዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው “ጣናን ለመታደግ የጋራ፣ የትብብር እና የፍቅር አረንጓዴ አሻራ ዘመቻ ወደ ጉና!” በሚል ርዕስ በአማራ ክልል የሚገኙ አስር የፌደራል መንግሥት ዩኒቨርሲቲዎችን አስተባብሮ
በደብረ ታቦር ጉና ተራራ፣ በደብረ ማርቆስ ጮቄ ተራራ፣ በባህር ዳር ቤዛዊት ቤተ-መንግስት፣ በጎንደር አውሮፕላን ማረፍያ፣ በደባርቅ ሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ እና ወሎ ጦሳ ተራራ
ላይ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር እንዲከናወን ማድረጉን አቶ ዳዊት አስታውቀዋል፡፡
በደቡብ ጎንደር ዞን የሚገኙ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚደርጉ የምርምር ሥራዎችን ማካሄድም ሌላኛው የዩኒቨርስቲው ተግባር ነው። በላይ ጋይንት የአፕል ልማት ምርምር ጣቢያ፣ በፋርጣ ጉና ጣና የተቀናጀ የመስክ ምርምርና ልማት ማዕከል አውዘት የምርምር ጣቢያ፣ በፎገራ የአሳ እርባታ ፕሮጀክት እና በስማዳ ምርምር ማዕከላት እያካሄደ እንደሚገኝ ነው የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ ያስረዱት።
ዘጋቢ:–መላኩ ሙሉጌታ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ


15
1 Share
Like
Comment
Share