
ፋሲል ከነማን ለመደገፍ የተዘጋጀው አምስት ኪሎ ሜትር ሩጫ በጎንደር ከተማ ተካሄደ።
ባሕር ዳር፡ ጥር 09/2013 ዓ.ም (አብመድ) በጎንደር ከተማ ባህረ ጥምቀቱን ለማክበር ከሀገር ውስጥ እና ከወጭ ሀገር የተገኙ እንግዶች፣ የከተማው ነዋሪዎች፣ የክለቡ ደጋፊዎች እና የሥራ ኃላፊዎች “ለፋሲል ከነማ እንሮጣለን በተግባር እንደግፋለን”በሚል መሪ ሃሳብ በተዘጋጀው ሩጫ ላይ ተሳትፈዋል፡፡

ሩጫውን በአንደኝነት ያጠናቀቀው መላኩ ሲሳይ እንደገለጸው “የክልላችን አርማ የሆነው የፋሲል ክለብ ለመደገፍ ሩጫለሁ ፤ በክለቡ ስም በመሮጥ አንደኛ በመውጣቴ ደስ ብሎኛል ብሏል።
ሌላው ተወዳዳሪ አምሳያው መኮንን የፋሲል ክለብ ኩራታችን በመሆኑ ሁሉም ክለቡን መደገፍ እንዳለበት ተናግረዋል። ክለቡን ለመደገፍም እንደተወዳደረ ገልጿል።
የፋሲል ከነማ ደጋፊዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት ኃይለማርያም ፈረደ ለፋሲል ክለብ የገቢ ማሰባሰብን ዓላማ ያደረገው ሩጫ በተገቢ መልኩ መከናወኑን ተናግረዋል።
ሩጫውን በዚህ ወቅት ማድረግ የተፈለገውም ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ ሀገረ ባህረ ጥምቀቱን ለመታደም የመጡ እንግዶች እንዲሳተፉ ለማስቻል ነው ብለዋል። ለውድድሩ ከተዘጋጀው የቲሸርት ሽያጭ እና ከስፖንሰር ክለቡን ማጠናከር የሚረዳ ገቢ መሰብሰቡን ተናግረዋል።
በተለይም የክለቡ ደጋፊ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ስታድየም ገብቶ ለመደገፍ በመቸገሩ በቂ ድጋፍ ሳይሰበሰብ መቆየቱን የተናገሩት አቶ ኃይለማርያም ዛሬ የተደረገው ሩጫ መነቃቃትን ፈጥሯል ብለዋል።

ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው – ከጎንደር
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ