
ጎንደር ለአስመራ ጥሪ አደረገች።
ባሕር ዳር፡ ጥር 05/2013 ዓ.ም (አብመድ)
በጎንደር በድምቀት ለሚከበረው የጥምቀት በዓል ለአስመራ ህዝብ ጥሪ መተላለፉን የጎንደር ከተማ አስተዳደር ባህል ቱሪዝምና ስፖርት መመሪያ አስታወቀ ።
የጥምቀት በዓል በጎንደር ከተማ በልዩ ድምቀት ይከበራል። ለዚህም ምክንያቱ ጎንደር የ44ቱ ታቦታት መገኛ፣ የነገሥታት መናገሻ፣ ታሪካዊ እና የአፄ ፋሲለደስ የባህር ጥምቀት ገንዳም መገኛ በመሆኗ ነው።

ባህረ ጥምቀቱን ምክንያት በማድረግ ወደ ጎንደር የሚሄዱ እንግዶችም በቦታው ሲገኙ ከሃይማኖታዊ ክዋኔ በተጨማሪ የጎንደርን ጥንታዊ፣ ታሪካዊ እና ባህላዊ ቅርሶችን እንዲጎበኙ ዝግጅት ተደርጓል። ለዚህም እንግዳ አክባሪው፣ ፍጹም ኢትዮጵያዊነት እሳቤ እና አመለካከት ያለው የጎንደር ህዝብ እንግዶችን ለመቀበል ቅድም ዝግጀት ማጠናቀቁን ነው መምሪያው ያስታወቀው።
ባህረ ጥምቀቱን ለማክበር ሲደረግ የነበረው ሰፊ ዝግጅት መጠናቀቁን የጎንደር ከተማ ባህል ቱሪዝምና ስፖርት መመሪያ አስታወቋል።
በመመሪያው የባህል ዕሴቶች እና ኢንዱስትሪ ልማት ቡድን መሪ ልዕልና ገብረ መስቀል እንዳሉት ለጥምቀት በዓል የቅድመ ዝግጅት ሥራ ሲከናወን ቆይቷል።

ቀድሞ የነበረው ጠንካራ ግንኝነት በሴረኛው ትህነግ ከተቋረጠ በኃላ የአስመራ ህዝብ ለጥምቀት በጎንደር እንዲገኝ የተላለፈ የመጀመሪያው ጥሪ መሆኑን የተናገሩት ቡድን መሪው ጥሪውም የነበረውን የቀደመ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ታሳቢ ያደረገ ነው ብለዋል።
የጋራ ባህል ያላቸው ሁለቱ ህዝቦች የጥምቀት በዓልን በጋራ ማክበራቸው በቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን፣ የአንድነት ስሜት እንዲጠናከር እና በትውልዱ ዘንድ የማይበጠስ ትስስር ለመፍጠር ያስችላል ብለዋል።
የጥምቀት በዓል ለጎንደር እና አካባቢው ማኀበረሰብ ልዩ ድምቀት አለው ያሉት አቶ ልዕልና የበዓሉን ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ ትውፊት ለመዘከር የአካባቢውን ባህልና ወግ የሚያስተዋወቁ ወጣቶች ፣ ጥበባዊ ሥራዎችን የሚያቀርቡ ባለሙያዎች፣ ኢግዚቢሽንና ልዩ ልዩ ሁነቶች መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
በበዓሉ ጥሪ ለተደረገለት የአስመራ ህዝብም ደማቅ አቀባበል እንደሚደረግ ታወቋል።
ዘጋቢ :- አዳሙ ሽባባው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ