
የትህነግ ቡድን ሚሊሻና ልዩ ኀይል ጥቅምት 26/2013 ዓ.ም በስደተኞች ካምፕ ላይ በከፈቱት ጥቃት የሰዎች ህይዎት ማለፉን በጎንደር ከተማ ጊዜያዊ መጠለያ የሚገኙ ኤርትራውያን ስደተኞች ተናገሩ።
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 21/2013 ዓ.ም (አብመድ) ኤርትራውያን ስደተኞቹ በትግራይ ክልል በሚገኙ ሽመልባና ህንጻጽ የስደተኞች ካምፕ የቆዩ ሲሆን የትህነግ ቡድን በነበሩበት የስደተኞች ካምፕ ላይ ግድያ መፈጸሙን ተከትሎ በህይዎት ተርፈው የመጡ መሆናቸውን ነግረውናል።
ኤርትራውያንን ጨምሮ ሌሎች በሽዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ላይ ቡድኑ ጥቅምት 26/2013 ዓ.ም በከፈተው ተኩስ ህይዎታቸውን ያጡ ሰዎች መመልከታቸውንም አስታውሰዋል።
አብዛኛዎቹ ቤተሰብ መስርተው ከ10 ዓመት በላይ የቆዩ ቢሆንም ቤተሰቦቻቸው በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ እንደማያውቁ ነው ከጥቃቱ ያመለጡ አስተያየት ሰጭዎች ያስረዱት።
ስደተኞቹ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ህይዎታቸውን ታድጎ ወደ ጊዜያዊ ማቆያው እንዳደረሳቸውም ነው ያብራሩት። ወደ ጎንደር ከተማ ከገቡበት ጊዜ አንስቶም የከተማዋ ነዋሪዎች ላደረጉላቸው ሰብዓዊ ድጋፍ አመስግነዋል።
ወደ ነበሩባቸው የስደተኛ ካምፖች መመለስ እንደማይፈልጉ የተናገሩት ስደተኞቹ የኢትዮጵያ መንግሥት አስፈላጊውን ሁሉ እንዲያመቻችላቸው ጠይቀዋል።
የሰላም ሚኒስቴር የሕግ ማስከበር ዳይሬክተር አንባየ ወልዴ መንግሥት ኤርትራውያን ስደተኞችን ለመርዳት ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
ዘጋቢ፡- ኃይሉ ማሞ- ከጎንደር
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ