
“የአማራ ብዙኀን መገናኛ ድርጅት ባለፉት ዓመታት ተለዋዋጭ የነበረውን የአትዮጵያ ፖለቲካ ላይ የተጫወተው ሙያዊ ድርሻ ጉልህ ነበር” የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ሙሉቀን ሰጥየ
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 13/2013 ዓ.ም (አብመድ) የአማራ ብዙኀን መገናኛ ድርጅት ሠራተኞችና መሪዎች ለተከታታይ ዓመታት በሀገር ግንባታና ሕግ የማስከበር ሥራ ላይ ላበረከቱት አስተዋፅኦ በተዘጋጀ የዕውቅና አሰጣጥ ሥነ ሥርዓት መድረክ ተካሂዶ ነበር፡፡
በዕውቅና አሰጣጡ ሥነ ሥርዓት ለተገኙ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች፣ ታዋቂ ሰዎች፣ ጥሪ ለተደረገላቸው እንግዶችና የተቋሙ ሠራተኞች የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ሙሉቀን ሰጥየ ያደረጉት ሙሉ ንግግርም ቀጥሎ ይቀርባል።
“የአማራ ብዙኀን መገናኛ ድርጅት ባለፉት ዓመታት ተለዋዋጭ የነበረውን የአትዮጵያ ፖለቲካ ላይ የተጫወተው ሙያዊ ድርሻ ጉልህ ነበር ፤ ዛሬ የተገናኘነው ባለፉት አመታት እንደ ድርጅት የነበረውን አስተዋጽኦ እንደ ማጠቃለያ የሚወስድ እና የህግ ማስከበር ላይ ለነበረን ድርሻ አብሮ እውቅና ለመስጠት የተዘጋጀ ነው፡፡
ብዙዎቻቹህ እንደምትረዱት እና እንደምትገነዘቡት የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት የህዝብ ተቋም ነው፡፡ ለአብዛኛው ህዝብ የሚሰራ የህዝብ ድምጽ የሆነ የሚዲያ ነው ፡፡ በየጊዜው በሚገጥመው ተለዋወጭ ሀገራዊ ሁኔታ ወስጥ ሆኖ ከህዝብ እምነት እና ፍላት ጎን የቆመ በጠዋትም በቀትርም ፤ በምሽትም የሚመጣ አውሎ ነፋስ እና ወጀብን እየተቋቋመ በሂደቱ እተማረ የመጣ ድርጅት ነው፡፡
የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት ሙያዊ መርህን ለማክበር ጥረት የሚያደርግ የጋዜጠኝነት ነጻነትን ከተጠያቂነት ጋር አጣጥሞ ለሰራተኞቹ የሚሰጥ ሁሌም ተማሪ እና አዳጊ፤ ባለሙያዎቹን አስልጥኖ እና አሳድጎ ሙያተኛ የሚያደርግ ለሃገራችን ሚዲያ ተቋማት የሰው ሃይል ያበረከተ በሚዲያ ነጻነት ዘርፍም አርዓያ የሚሆን ድርጅት ነው፡፡
የክልል ሚዲያ ቢሆንም ለሀገር ግንባታ እና ለመላው እትዮጲዊያን ሁሉ የሚዲያውን አገልግሎት ለማሳደግ እየሰራ ይገኛል፡፡ የሀሳብ እና ቋንቋ ብዝሃነትን ቀድሞ የተረዳ እና ተግባራዊ እያደረገ ነው፡፡
በክልሉ ውስጥ አገልግሎት ላይ የሚገኙ ቋንቋዎችን በሁሉም ጣያቢያዎቹ እና ህትመቶቹ በመጠቀም የሚሰራ ከክልሉ ውጭም ቅርንጫፎችን በመክፍተ እና ስምሪቶችን በመስጠት ብዝሃ አገልግሎት እየሰጠ ነው፡፡ በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡
ድርጅታችን የሃሳብ ብዝሃነትን በውል የሚገነዘብ እና የሚያከብር ፣ የተለያዩ አመለካከቶችን በሚዲያው እንዲስተናገዱ የሚያደርግ እና ህዝቡ የወደደውን ሃሳብ እንዲመርጥ እድል የፈጠረ ነው፡፡ በቀጣይም በሰለጠነ መንገድ የተለያዩ ሃሳቦች ወደ ህዝብ እንዲደርሱ ማድረጉን ይቀጥላል፡፡
በአብመድ ጣቢያዎች እና ህትመቶች ተማሪውና ሊህቃኑ ፤ከተሜው እና ሰፊው የገጠር ኗሪ ፤ ወላጆች እና ልጆች ፤ ጠያቂዎች እና ተጠያቂዎች ሁሉም የሚናገሩበት እና የሚደመጡበት የህዝብ ሚዲያ ነው ፡፡
ድርጅታችን በርካታ ሰራተኞቹን እና አመራሮቹን አቅም ለማሳደግ የትምህርት እድል የሚሰጥ “በሰው የሚሰራ” እንዲሁም “ለሰው የሚሰራ” የሚዲያ ተቋም ነው፡፡ በአሰራሩ ግልጽ እና በተቋሙ ጉዳዮች ሁሉም ስራተኛ እንዲሳተፍ የሚያደርግ ሁሉንም ባለቤት የሚያደርግ ስራ ይሰራል፡፡
አማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት ከ2008 ለውጥ በፊት ህዝብ መብቶቹን እና ፍላጎቶቹን የማቅረብ ባህል ያሳደገ እንደሁም በቀጥታ ስርጭት በሚተላለፍ ዝግጅት አመራሩን ፊት ለፊት የሚሞግት እና ሃሳብ ነጻነትን የሚያሳድግ ተግባር ስርቷል፡፡ በለውጡ ዘመን ህዝቡ በአደባባይ ይዟቸው የወጣቸው ጥያቄዎችን በከተሞች መድረክ እና በሌሎች ዝግጅቶቻችን ከለውጥ ቀድሞ ህዝቡ ሲያነሳቸው ነበር፡፡
በለውጡ ጊዜ የህዝብ ማዕበል ወደ አደባባይ በወጣበት ጊዜ የህዝቡን ጥያቄዎች ለአለም ያስተዋወቀ አብመድ ነው፡፡ በህዝባዊ አመጹ በነጻነት የሚንቀሳቀሱት የአብመድ ተሸከርካሪዎች እና ባለሙያዎች ብቻ ነበሩ፡፡ በሰልፎቹ የሚገኙት ወጣቶቹ የድጅታችን ሰራተኞች ከሆነ መንገድ ከፍተው ያሳልፉ ነበር፡፡ በየትኛውም ህዝባዊ አመጽ በነበረበት የገቡ ጋዜጠኞች ህዝቡ ከጎናቸው ሆኖ ሁለንተናዊ ድጋፍ ያደርላቸው ነበር፡፡
ከለውጥ በፊት እና ለውጡ እንደመጣ በወቅቱ ከነበሩ የመንግስት ኃላፊነት ከያዙ አካላት ተደጋጋሚ ጫና ማስጠንቀቂያ ደብዳቤ እና ስብሰባዎች ላይ ወደ ዛቻ ድረስ የሚቃረቡ ጭቅጭቆች ነበሩ፡፡ እነሱንም አልፈናቸዋል፡ለውጡ ከመጣ በኋላ ለውጡ እንዴት ውጤታማ ይሁን የሚሉ ሃሳቦች የተንጸባረቁባቸው እውቀታዊ ትንታኔዎች በተለያዩ አካላት እንዲቀርቡ የማድረግ ስራ ተስርቷል፡፡
ለውጡ ከመጣ በኋላ ከገጠሙን እንቅፋቶች መካከል አንዱን ባነሳ ባህር ዳር ላይ የነበረውን ለጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክር ዐቢይ አመራር የተደረገውን የድጋፍ ስልፍ በቀጥታ ስርጭት ለማስተላለፍ ዝግጅት አጠናቀን ሁሉም ነገር ከላቀ በኋላ አማራ ቴቪ ከናይል ሳት ሳተላይት እንዲወርድ ተደረገ ፡፡
ችግሩን ለመፍታት ሌሊቱን ከግብጽ ሀገር ከሚገኘው ናይል ሳት አመራሮች ጋር በስልክ በኢሜል እና በተለያዩ አማራጮች ተነጋገርን ውይይት አደረግን ግን ችግሩን ሊፈቱት አልፈለጉም ፤ በወቅቱ በግብጽ የኢትጰያ አምባሳደር ጭምር ስርጭቱ እንዲለቀቅ ጥረት አደረጉ፤ የድጋፍ ቀጥታ እንዳይተላለፍ የተሸረበ ሴራ ስለነበር አልተሳካም፡፡ቀጥታ ስርጭቱንም በሌሎች ሚዲያዎች እና በአዲሱ ሚዲያ እንዲተላለፍ ተደረገ፡፡
የቀጥታ ስርጭቱ እንደተጠናቀቀ ወዲያዉኑ የአማራ ቴሌቪዥን ስርጭቱ እንዲመለስ ተደረገ፡፡ይህም ብቻ አይደለም ድርጅታችን ከዚያ በፊትም ሚዲያው ለቴክኖሎጂ ግዥዎች የውጭ ምንዛሬ አለማግኘት እና ማዘግየት እንዲሁም ሁሉ አቀፍ ጫና ይደረግበት ነበር፡፡
ክቡራትና ክቡራን
ከለውጥ በኋላ ለኢኮኖሚያዊ እድገት ከፍተኛ ሚና የሚወጡ በርካታ ዶክመንታሪዎች፣መጣጥፎች እና የዜና ዘገባዎች፣ የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጉዳዮች፤የህዝብ ጥያቄዎች መዋቅራዊ ምላሽ እንዲገኙ የሰከኑ ውይይቶች እንዲኖሩ ስራዎችን ስርቷል፡፡ ስላም እና መረጋጋት እንዲመጣ የሚያስችሉ ሃሳቦች፤ የአማራ ህዝብ ጥያቄዎች አና የህዝቡ እሴቶች፣ የፍትህ ስርዓቱ ላይ የሚነሱ የህዝብ ጥያቄዎች እና የመፍትሄ መንገዶቹ እንዲሁም ገጽታ ገንቢ የቀጥታ ስርጭት ስራዎች ከፍኛ ትኩረት ተሰጥቷቸው ተሰርተዋል፡፡
ከለውጥ በኋላ ባጋጠመው ሀገራዊ እና ክልላዊ ፈታኝ የቀውስ ወቅቶች ፤ የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች፣ ግጭቶች፣መፈናቀሎች እና ግድያዎች የድርጅታችን ጋዜጠኞችና አመራሮች ከፊት ይገኙ ነበር በሁሉም ቦታ ቀድመው ይደርሳሉ ፡፡ የየአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት ሰራተኞች በየትኛውም ፈተና እና ችግር ውስጥ ቀድሞ ደራሾች ናቸው፡፡
በቅርቡ በተከሰተው የትህነግ ቡድን ህገወጥነት ተከትሎ በህግ ማስከበር ወቅት ሰራተኛውን ሰብሰብን ዝግጅት እንዴት እናድረግ የዘገባ ስራችንን እንዴት እንስራ የሚለውን የጋራ ለማድረግ ምክክር አድርገን ነበር ፡፡ በዚህ ወቅት ለሰራተኛው አንድ ሃሳብ አቀረብን ወደ ጦር ግንባር ጋዜጠኞች እናሰማራለን ሁሉም ራሱን ያዘጋጅ የሚል አጭር ሀሳብ ቀጥሎ የሰራተኛው ሀሳብ ተደመጠ ሁሉም የሚለው እኔን ላኩኝ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት በሁሉም ግንባሮች ቀድሞ የገባው አብመድ ነበር ፡፡
በአጠቃላይ አብመድ ውስጥ ያለው ተነሳሽነት እና ታታሪነት የድርጅቱ ብቻ ሳይሆን የክልሉም የሀገርም እሴት ስለሆነ ለድርጅቱ እና ለሰራተኞቹ እድገት ሁሉም ድጋፍ እና እገዛ እንዲያደርግ በዚህ አጋጣሚ ጥሪ ማቅረብ እፈልጋለሁ፡፡
በዛሬው እለት የምንሰጠው እውቅና እና ምስጋና በተለያዩ ቦታዎች እና የስራ ዘርፎቹ ለሚሰሩ ለሁሉም የድርጅታችን ሰራተኞች እና አመራሮች ሲሆን ይህም ሩጫችንን ስለጨረስን ሳይሆን በቀጣይ የሚበጠቅብንን ዘርፈ ብዙ ስራ ስለሚየበቅብን ለቀጣይ ለላቀ አበርክቶ ለመዘጋጀት እና እንደ መነሻ ለመጠቀም ነው፡፡
በመጨረሻም ድርጅታችን በቀጣይ በሁለንተናዊ እድገት እና በአዲስ መንገድ በአዲስ ገጽታ፣ ስያሜ እና ብራንድ ለመምጣት ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡
ለህብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
አመሰግናለሁ”
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ