
“ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋም ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 04/2013 ዓ.ም (አብመድ) ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋም ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በአየር ንብረት ላይ ባተኮረው የቪዲዮ ኮንፍረንስ ላይ ተሳትፈዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በውይይቱ ባስተላለፉት መልዕክት ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም መጠነ ሰፊ ስራዎችን እየሰራች መሆኗን አብራርተዋል።
ለጉዳዩ በተሰጠው ትኩረትም በሀገር አቀፍ ጀረጃ የችግኝ ተከላ ስራ መሰራቱን እና ችግኞችን መንከባከቡም መቀጠሉን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ነውም ብለዋል። በዚህም መሠረት እስከ ፈረንጆቹ 2030 ከካርቦን ልቀት ነጻ የሆነ ኢኮኖሚን ለመገንባት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመከላከል ወሳኝ ስራ መስራቷን ገልጸዋል። በ10 አመት የልማት እቅድም አስተማማኝ ኢኮኖሚ ለመገንባት ማቀዷን ነው ያነሱት።
ከብልጽግና ፓርቲ የማህበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ እንዳመላከተው የፓሪስ ስምምነትን በማክበር ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቀነስ የ15 አመት እቅድ መያዟን ተናግረዋል። በእቅዱ 18 ዘርፎች መለየታቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ግብርና፣ የደን ልማት፣ ጤና እና ትራንስፖርት መሆናቸውን አብራርተዋል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ