
በ2 ዓመታት ይጠናቀቃል የተባለው ፋብሪካ ተጨማሪ 2 ዓመታትን ጠይቀቋል ለምን?
ባሕር ዳር፡ ኅዳር 12/2013 ዓ.ም (አብመድ) የውጭ ምንዛሬ እጥረት የአባይ ሲሚንቶ ፋብሪካን በተያዘለት ጊዜ እዳይጠናቀቅ አድርጎታል፡፡ የአብመድ የጋዜጠኞች ቡድን በቦታው ተገኝቶ እንደታዘበው አሁን ላይ የሠራተኞች ማረፊያ፤ የመጋዘን ሕንጻዎች እና ለግንባታ የሚሆን መሬት የማመቻቸት (ሌቭሊንግ) ሥራ ብቻ ነው የተከናወነው። በዚህ ጊዜ አጠቃላይ የፕሮጀክት ሥራው መገባደጃ ላይ መድረስ የነበረበት የአባይ ሲሚንቶ ፋብሪካ እስካሁን የተጠናቀቀው አጠቃላይ የፕሮጀክት ሥራው 15 በመቶ ነው።
የአባይ ኢንዲስትሪያል አክሲዮን ማኅበር በእንጨትና ብረታብረት፣ በአልባሳትና ጨርቃጨርቅ እንዲሁም በሲሚንቶ ዘርፎች ለመሰማራት በአማራ ክልል መንግስትና በግል ባለሀብቶች አማካኝነት የተቋቋመ ማኅበር ነው።
ማኅበሩ በአማራ ክልል ከሚገነባቸው ትላልቅ ፕሮጀክቶች መካከልም ደጀን ወረዳ ላይ እየተገነባ ያለው የሲሚንቶ ፋብሪካ አንዱ ነው። ለፕሮጀክት ግንባታው 8 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ወጪ የሚደረግበት ይህ ፋብሪካ በቀን 7 ሺህ 500፣ በዓመት ደግሞ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ቁምጣ ሲሚንቶ ማምረት የሚችል ነው። ወደ ስራ ሲገባም ለክልሉ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ምንጭ ይሆናል፣ ለብዙዎች የሥራ እድል ይፈጥራል፣ አሁን በሀገሪቱ ያለውን የሲሚንቶ እጥረት በመፍታትም ጉልህ ሚና እንደሚጫወት ነው በዓባይ ኢንዱስትሪያል አክሲዮን ማኅበር የሲሚንቶ ኮርፖሬት አስተባባሪ ዳኛቸው በየነ የተናገሩት።
ደጀን ወረዳ በአማራ ክልል ለሲሚንቶ ፋብሪካ ሁሉም የማዕድን አይነቶች በቅርብ ርቀት ከሚገኙባቸው ቦታዎች መካከል አንዱ ነው። ዓባይ አክሲዮን ማኅበርም አመቺነቱን በጥናት አረጋግጦ ነው ፋብሪካውን በ123 ሄክታር መሬት ላይ እየገነባ ያለው። እንደ ላይምስቶን፣ ጅብሰም፣ ቀይ አፈር (ክለይ) እና ሲልካ ማዕድናት በአባይ በርሃ አካባቢዎች በስፋት ይገኛሉ። ኢንዱስትሪው ደጀን ላይ እንዲገነባም ቀዳሚ ምክንያት ነው። ፋብሪካው ከሚጠቀማቸው ግብዓቶች መካከል 70 በመቶውን ድርሻ የሚወስደው ላይምስቶን የሚባለው ማዕድን ነው። የዚህ ማዕድን ክምችት ከሌሎቹ ማዕድናት ሁሉ ከፍተኛ ነው።
አቶ ዳኛቸው እንዳሉትም ከ70 ዓመት በላይ ለፋብሪካው ግብዓት መሆን እንደሚችል በጥናት ተረጋግጧል። ይሁን እንጂ የኢንዱስትሪው አጠቃላይ የፕሮጀክት ሥራውና የግንባታ እንቅስቃሴው በእቅዱ መሠረት እየተከናወነ አይደለም። በተያዘለት ጊዜ እንደማይጠናቀቅም አቶ ዳኛቸው አረጋግጠዋል። አጠቃላይ የፋብሪካው የፕሮጀክት ሥራ በ24 ወራት ውስጥ (በመጪው ጥር/2013 ዓ.ም) ተጠናቅቆ ሥራ እንደሚጀምር ነበር በግንባታ ማስጀመሪያው ጊዜ የተገለጸው። አሁን ደግሞ የፋብሪካውን ፕሮጀክት ለማጠናቀቅ ተጨማሪ 22 ወራት ይጠይቃል ብለዋል አስተባባሪው ለአብመድ በሰጡት ማብራሪያ።
ለፕሮጀክቱ መጓተት በዋናነት የተነሳው ምክንያት የውጪ ምንዛሬ እጥረት ነው። ለፋብሪካው ግንባታ የሚያስፈልጉ አብዛኛዎቹ ቁሳቁስና ማሽኖች ከአውሮፓ የሚቀርቡ ናቸው። ለዚህ ከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ የሚያስፈልግ ሲሆን የውጪ ምንዛሬ ማግኘት አስቸጋሪ ስለመሆኑ አንስተዋል። ከምንዛሬ እጥረቱ ውጭ ፕሮጀክቱን በፍጥነትና በጥራት ለማከናወን ትኩረት አግኝቷል፡፡ በዚህም ለግንባታ ሥራው ውል የያዙ የግንባታ ተቋራጭ፣ የማሽኖችና ሌሎች ቁስቁስ አቅራቢ እንዲሁም የግንባታ አማካሪ ድርጅቶች የረጅም ጊዜ ልምድና ዓለም አቀፍ እውቅና ያላቸው ናቸው።
በተለይ ከኳሪን ሳይት እስከ ፋብሪካው ሥራ ላይ የሚውሉ የማሽን እቃዎችን ለማቅረብ የውል ስምምነት የተፈራረመው የዴንማርክ ድርጅት በዘርፉ ከ140 ዓመታት በላይ የሠራ መሆኑን አረጋግጠውልናል። የግንባታ ሥራውን ደግሞ ከዚህ በፊት በተለያዩ ሀገራት በሲሚንቶ ፋብሪካና ሌሎች ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች ግንባታ ላይ የተሳተፈና እውቅና ያለው የቻይና ድርጅት ነው የተረከበው።
በተመሳሳይ መልኩ ከ45 ዓመታት በላይ በተለይም በሲሚንቶ ፋብሪካው ዘርፍ የማማካር ልምድያለው ሆልቴክ የተባለ የህንድ ድርጅት ይዞታል። ሌሎችም የአውሮፓ ድርጅቶች የማሽን ተከላው ዓለም አቀፍ ደረጃውን ይዞ እንዲጠናቀቅ የቁጥጥር ሥራና ተጨማሪ አማካሪ ስለመኖሩም አንስተዋል። እነዚህ ዓለም አቀፍ የግንባታ ዘርፉ ድርጅቶች ፋብሪካውን ጥራት ያለው፣ የተሻለና ዘመኑ የደረሰበትን ቴክኖሎጂ የሚጠቀም እንደሚያደርጉት ማኅበሩ አምኖባቸዋል።
ያጋጠመውን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለመፍታት የፌዴራል መንግስት አዲስ መፍትሄ ተግባራዊ እያደረገ ነው፡፡ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሆኖ በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የሚመራ የማክሮ ቡድን በተለይ በሲሚንቶ ላይ የተከሰተውን ችግር መሠረታዊ ምክንያት አጥንቷል። ሌሎች የሲሚንቶ ፋብሪካዎችን ጨምሮ በግንባታ ሂደት ላይ የሚገኘው የዓባይ ሲሚንቶ ፋብሪካም ችግሩ እንዲፈታላቸው ውሳኔ ተላልፏል።
ከውሳኔው መካከል በቂ ምንዛሬ እንዲያገኙ ማድረግ አንዱ ነው። የውጪ ምንዛሬ እንዲያገኙ የሚደረገው ደግሞ እንደተለመደው ከባንኮች ሳይሆን ለአስቸኳይ (ለኢመርጀንሲ) ተብሎ ከተቀመጠ የውጪ ምንዛሬ ላይ ነው። ለማኅበሩ ቅድሚያ 20 ሚሊዮን ዶላር በሂደት ደግሞ 62 ሚሊዮን ዩሮና 70 ሚሊዮን ዶላር እንዲሰጠው ተወስኗል። 20 ሚሊዮን ዶላሩ እንደተለቀቀለትም አስተባባሪው ዳኛቸው አስታውቀዋል። ቀሪው ደግሞ በሂደት እንደሚለቀቅለትም አብራርተዋል።
በዚህ ጊዜ የፕሮጀክት ሥራው እየተከናወነ ሲሆን በተቻለ መጠን በፍጥነት ለማጠናቀቅ ልዩ ትኩረት በመስጠት እንደሚሠራበትም አመላክተዋል። ይሁን እንጂ ለማጠናቀቅ ተጨማሪ 22 ወራት እንደሚያስፈልግ ነው አቶ ዳኛቸው የተናገሩት። የሆነው ሆኖ በነዚያ ተጨማሪ 22 ወራት ግንባታው ይጠናቀቅ ይሆን? አብመድም እየተከታተለ መረጃውን ያደርሳል።
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ