
ለስግብግቡ ጁንታ ግፍ እስትንፋሱ፣ ጭካኔ ነፍሱ ነው። ጀግናው የመከላከያ ሠራዊታችን ሽራሮን ሲቆጣጠር፣ እጅና እግራቸውን የፊጥኝ ታሥረው የተረሸኑ የመከላከያ አባላትን አግኝቷል። ጭካኔው ልብ ሰባሪ ነበር። ዓላማው ኢትዮጵያን መስበር ነው። አላወቁም ከአልማዝ የጠነከረች መሆኗን። ዓላማው ሠራዊታችንንና ሕዝቡን አስቆጥቶ ለበቀል ርምጃ ማነሣሣት ነው። አላወቁም ልበ ሰፊ ሕዝብና ሠራዊት እንዳለን።
በየቦታው ስንደርስ ከዚህ የከፋ ጭካኔና ግፍ ሊገጥመን ይችላል። ይህ ግን ለዚህ ጁንታ የመጨረሻው ነው። ጥንቃቄያችን ‘ሙት ይዞን እንዳይሞት’ ነው። መፍጠን አለብን፤ የተረፉትን ለመታደግና ግፍ የተፈጸመባቸውንም ለዓለም ለማጋለጥ።
የምዕራቡን የትግራይ ክልል ቀጣና ነጻ ወጥቷል። በዚያ ቀጣና ሠራዊቱ ሰብዓዊ ርዳታና አገልግሎት እየሰጠ ነው። ነጻ ባወጣቸው አካባቢዎች ሕዝቡን እየመገበ፣ እያከመና እየተንከባከበ ነው።