ከ15 በላይ ወረዳዎችን ያሳተፈው 23ኛው የደቡብ ጎንደር ዞን ወረዳ አቀፍ የባሕል ስፖርት ውድድር ተጠናቅቋል።
በማጠናቀቂያ መርሐ ግብሩ ላይ አስተያየቷን ለአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) የሰጠችው የደብረ ታቦር ከተማ ነዋሪ እና የባሕል ስፖርት ትግል ተወዳዳሪዋ ወጣት አበበች ተስፋ የሁለት ልጆች እናት ናት።
በመክፈቻ መርሐ ግብሩ ላይ አሸናፊ እንደምትኾን ቃል ገብታ የነበረችው ወጣቷ፣ ቃሏን በተግባር በማረጋገጥ ለአምስተኛ ጊዜ በትግል የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ መኾን ችላለች።
የልጅ እናት መኾን ከስፖርት ውድድር እንደማያግዳት የገለጸችው ወጣት አበበች፣ ልጆቿ ለአሸናፊነቷ ትልቅ ብርታት እና ምክንያት እንደኾኗት ተናግራለች።
ያገኘችውን የወርቅ ሜዳሊያ በእቅፏ ለያዘችው ልጇ ያጠለቀች ሲኾን፣ “ወርቆቼን ለወርቅ ልጆቼ ማጥለቄ ለቀጣይ ስኬቴ ትልቅ መነሳሳት ይፈጥርልኛል” ብላለች።
በቀጣይም በእንጅባራ ከተማ በሚካሄደው 24ኛው የአማራ ክልል የባሕል ስፖርት ውድድር ላይ ተሳትፋ ሀገሯን እና ክልሏን በብቃት ለመወከል ጠንካራ ዝግጅት እንደምታደርግ ገልጻለች።
በተመሳሳይ ውድድር የወርቅ ሜዳሊያ ያስመዘገበው የስማዳ ወረዳ ነዋሪ ወጣት ጌታሰው አለበል በበኩሉ፣ ለስኬቱ ለባሕል ስፖርት ያለው ጥልቅ ፍቅር እና የቤተሰቦቹ ድጋፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቅሷል።
አክሎም፣ በዘርፉ በሙያው የሠለጠኑ አሠልጣኞች ቢመደቡ እና የተሻለ ትኩረት ቢሰጠው የሀገሩን ሰንደቅ ዓላማ በዓለም አቀፍ መድረክ ከፍ አድርጎ የማሳየት ጽኑ ፍላጎት እንዳለው አብራርቷል።
በመዝጊያ መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የደቡብ ጎንደር ዞን ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ ተወካይ ኀላፊ ተፈሪ አክሎግ፣ ለተከታታይ ቀናት የተካሄደው ውድድር ፍጹም ስፖርታዊ ጨዋነት የታየበት እና ዘርፉን ለማነቃቃት መልካም ዕድል የፈጠረ መኾኑን ገልጸዋል።
እንደ ገበጣ፣ ትግል እና ፈረስ ጉግስ ያሉ ሀገር በቀል ቅርሶች ከዘመናዊ ስፖርቶች ባልተናነሰ ትኩረት እንዲያገኙ መምሪያው ከአጋር አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሠራም አረጋግጠዋል።
የደቡብ ጎንደር ዞን አሥተዳደር ግብርና መምሪያ ምክትል ኀላፊ እና ተወካይ አሥተዳዳሪ አባተ ሽባባው በበኩላቸው፣ የባሕል ስፖርት የመልካም እሴቶች ማጠናከሪያ እና የማንነት መገለጫ መኾኑን አንስተዋል።
ስፖርቱ ከአካል ብቃት ባሻገር ማኅበራዊ ትስስርን ለማጠናከር ያለውን ፋይዳ ጠቅሰው፣ ዘርፉን ይበልጥ ለማሳደግ ሰላምን የማጽናት እና የሠለጠኑ ባለሙያዎችን የማሰማራት ሥራ በትኩረት እንደሚከናወን ተናግረዋል።
መርሐ ግብሩ በውድድሩ ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተወዳዳሪዎች የሽልማት እና የዕውቅና ሰርተፊኬት በመስጠት ተጠናቅቋል።
#አሚኮ #ስፖርት🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ኅዳር_07_2019_ዓ_ም
ዘጋቢ፦ ተክለብርሃን ፈንታ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!



