በ16 ቡድኖች መካከል ለሁለት ሳምንታት ሲካሄድ የቆየው የወልድያ ከተማ አቀፍ የፉትሳል ውድድር በአዳጎ ቡድን አሸናፊነት ተጠናቅቋል።
ውድድሩን የከተማዋ ባሕል፣ ቱሪዝም አና ስፖርት መምሪያ ከየጁ ፍሬ አካዳሚ ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ነው።
የየጁ ፍሬ ስፖርት አካዳሚ መሥራች እና አሠልጣኝ አረፈዓይኔ ሙሉጌታ እንደገለጹት ውድድሩ የወልድያ ከተማን የእግር ኳስ እንቅስቃሴ ለማነቃቃት እና የከተማውን ስፖርት ክለብ ወደ የቀደመ ከፍታው ለመመለስ የሚያስችሉ ታዳጊዎችን ብቃት ለመፈተሽ ያለመ ነው።
የወልድያ ከተማ ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ ነፃነት አምበሳው በበኩላቸው መሰል ውድድሮች ወጣቶችን ከቁዘማ ለማንቃት፣ በስፖርት የጎለበተ ትውልድ ለመፍጠር እና የከተማዋን ክለብ አቅም መልሶ ለመገንባት ያላቸውን አስፈላጊነት ጠቅሰዋል።
የእግር ኳስ እና ሌሎች ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ወደፊትም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።
የወልድያ ስፖርት ክለብ የቀድሞ ተጫዋች እና የውድድሩ አሸናፊ የአዳጎ ቡድን አባል ተስፋዬ ምሥጋናው ክለቡ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ
የነበረውን ንቁ ተሳትፎ በማስታወስ ይህ ውድድር በከተማዋ ሰፍኖ የነበረውን የስፖርት መቀዛቀዝ ወደ አዲስ መነቃቃት ያሻገረ መኾኑን ገልጿል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!



