ትእግስት አሰፋ የዓለም አትሌቲክስ የዓመቱ ምርጥ አትሌት እጩ ኾነች።

0
11
የዓለም አትሌቲክስ በሁለቱም ጾታዎች ይፋ ባደረገው የ20 እጩዎች ዝርዝር ውስጥ ኢትዮጵያዊቷ የማራቶን አትሌት ትእግስት አሰፋ በብቸኝነት ተካታለች።
ትእግስት ለዚህ እጩነት የበቃችው በ2026 የለንደን ማራቶን በ2 ሰዓት ከ15 ደቂቃ ከ41 ሰከንድ በሴቶች ብቻ የዓለም ክብረወሰን በመስበር ባስመዘገበችው ድል እና በበርሊን ማራቶን ባሳየችው አስደናቂ ብቃትና ጽናት ነው።
በበርሊን ውድድር ወቅት ከ40 ኪሎሜትር በኋላ እግሯ ላይ ጉዳት ቢደርስባትም ውድድሩን በአሸናፊነት ማጠናቀቅ ችላለች። አትሌቷ በ2023ም «ከስታዲየም ውጭ» በሚለው ዘርፍ የዓመቱ ምርጥ አትሌት ሆና መመረጧ ይታወሳል።
የሴቶች እጩዎች ዝርዝር፡ በሴቶች ዘርፍ ከትእግስት አሰፋ በተጨማሪ ኤግነስ ንጌቲች (ኬንያ)፣ አውዲ ዌሮ (ስዊዘርላንድ)፣ ማሳይ ሩሰል፣ ሜሊሳ ጀፈርሰን እና ቼዝ ጃክሰን (አሜሪካ)፣ ያን ዢዪ (ቻይና)፣ ካምሪን ሮጀርስ (ካናዳ)፣ ማሪያ ፔሬዝ (ስፔን) እንዲሁም ማሪሌዲ ፓውሊንሆ (ዶሚኒካን ሪፐብሊክ) ታጭተዋል።
በወንዶች ዘርፍ ኮለን ኬቢናትሺፒ (ቦትስዋና)፣ ሴባስቲያን ሳዌ (ኬንያ)፣ ኬኔት ቤድናሬክ እና ጃኮብ ታርፕ (አሜሪካ)፣ ክርስቲያን ቼህ (ስሎቬኒያ)፣ አንዲ ዲያዝ ሄርናንዴዝ (ጣሊያን)፣ አሊሰን ዶስ ሳንቶስ (ብራዚል)፣ ሞንዶ ዱፕላንቲስ (ስዊድን)፣ ጆሽ ኬር (ታላቋ ብሪታንያ) እና ሩመሽ ታራንጋ (ስሪላንካ) ተካተዋል።
ኢትዮጵያ ቀደም ሲል በወንዶች በኃይሌ ገብረስላሴ፣ ቀነኒሳ በቀለ እና ታምራት ቶላ፤ በሴቶች ደግሞ በመሰረት ደፋር፣ ገንዘቤ ዲባባ እና አልማዝ አያና አማካኝነት የዓመቱ ምርጥ አትሌት ክብርን ተጎናጽፋለች።
አሸናፊው በደጋፊዎች (25%)፣ በሚዲያ ባለሙያዎች (25%)፣ በአትሌቶች (25%) እና በዓለም አትሌቲክስ ቤተሰቦች (25%) ድምፅ የሚወሰን ሲሆን፣ የሽልማት ሥነ-ሥርዓቱ ከ19 ቀናት በኋላ በሞናኮ ይከናወናል።
ዘጋቢ፡ ሐናማርያም መስፍን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here