ማንችስተር ዩናይትድ ከማንችስተር ሲቲ የሚያደርጉትን ይህን ታላቅ ጨዋታ የዩናይትዱ ሜዳ ኦልድ ትራፎርድ ያስተናግዳል። ቡድኖቹ በሁሉም ውድድሮች ለ199ኛ ጊዜ የሚገናኙ ሲኾን፣ ማንችስተር ዩናይትድ 81 ጨዋታዎችን በማሸነፍ የታሪክ የበላይነቱን ይዟል።
በአዲሱ አሠልጣኛቸው ኤንዞ ማሬስካ የሚመሩት ማንችስተር ሲቲዎች በሊጉ ባደረጓቸው ባለፉት ሦሥት ጨዋታዎች ሙሉ ዘጠኝ ነጥብ በመሰብሰብ በጥሩ መነቃቃት ላይ ይገኛሉ።
በሌላ በኩል በማይክል ካሪክ የሚመራው የምሽቱ ባለሜዳ ማንችስተር ዩናይትድ፣ በሊጉ ባደረጋቸው ባለፉት ሦሥት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባው ዘጠኝ ነጥብ 4 ነጥብ ብቻ በማሳካቱ ዛሬ ከባድ ፈተና ይጠብቀዋል።
ሁለቱ ቡድኖች በሳምንቱ አጋማሽ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ካስመዘገቡት ድል ማግስት የሚገናኙ መኾኑ ደግሞ ለጨዋታው ተጨማሪ ድምቀት ሰጥቶታል።
ምሽት 12:30 ላይ በሚጀመረው በዚህ ጨዋታ፣ በይፋዊ አሰላለፍ በኩል በማንችስተር ዩናይትድ ማርከስ ራሽፎርድ ወደ ቋሚ ሥብሥብ ይመለሳል ተብሎ ይጠበቃል። በአንጻሩ ማኑኤል ኡጋርቴ፣ አማድ ዲያሎ፣ ማቲያስ ደ ሊክት እና ካርሎስ ባሌባ ከጨዋታው ውጭ ኾነዋል።
በውኃ ሰማያዊዎቹ ማንችስተር ሲቲ በኩል አሠልጣኝ ኤንዞ ማሬስካ የክንፍ ተጫዋቻቸውን ጄሬሚ ዶኩ በጉዳት ምክንያት እንደማያሰልፉ ሲያረጋግጡ፤ ኒኮ ኦራይሊ እና ማቴውስ ኑኔስ ከጉዳት መልስ ለጨዋታው ዝግጁ መኾናቸው ታውቋል።
ከዚህ ጨዋታ ቀድሞ ከቀኑ 10:00 ላይ ኮቨንተሪ ሲቲ ከብራይተን ጋር የሚጫወቱ ይኾናል።
በዳናይት ሲሳይ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!



