ለ 2 ቀናት በሚካሄደው የዋንዳ ዲያመንድ ሊግ የብራሰልስ ፍጻሜ ከሚጠበቁ ርቀቶች መካከል የሴቶች 800 ሜትር
ይገኝበታል፡፡
በዚህ ርቀት የማለፊያ ነጥብ ያገኙ 2 ኢትየጰያውያን አትሌቶች እንደሚሳተፉ ቀድሞ የወጣው ዝርዝር ቢያመላክትም ጽጌ ድጉማ በተመሳሳይ የማለፍ ዕድል ባገኘችበት 1ሺህ 500 ሜትር የምትሳተፍ ይኾናል፡፡
በ800 ሜትር አስቀድሞ አስደናቂ ተፋላሚዋ ኬንያዊቷ ሊሊየን ኦዲራ በጉዳት ምክንያት ከርቀቱ ውጭ መኾኗ ይታወሳል፡፡ በዚህም ምክንያት ፍልሚያው በኢትዮጵያ፣ በስዊዘርላንድ፣ በኔዘርላንድስ እና በደቡብ አፍሪካ አትሌቶች መካከል ይኾናል ተብሎ ሲጠበቅ ጽጌ ከውድድሩ ውጭ ኾናለች፡፡
ይህ የኾነበት ምክንያት ደግሞ 2ቱ ርቀቶች የሚደረጉበት የሰዓት ልዩነት ከ1 ሰዓት ያነሰ በመኾኑ ነው፡፡ በዚህም ኢትዮጵያዊቷ አትሌት 1ሺህ 500 ሜትርን ምርጫዋ አድርጋለች፡፡
ጽጌ በሲሌሲያ ዳይመንድ ሊግ በ1ሺህ 500 ሜትር የዓመቱን ፈጣን ሰዓት እና የግል ምርጥ ሰዓቷን 3 ደቂቃ ከ55 ሰከንድ ከ06 ማይክሮ ሰከንድ በመግባት ማሸነፏ እና ማስመዝገቧ ይታወሳል፡፡
በርቀቱም ብርቄ ሀየሎም እና ጽጌ ድጉማ የዳይመድ ፈርጡን ለማግኘት ፉክክር ሲያደርጉ የእንግሊዟ ጆርጂያ ሀንትር ቤል እና የአውስትራሊያዋ ጀሲካ ሁል ሌሎቹ ተፎካካሪዎች ናቸው፡፡
በ800 ሜትር የወቅቱ 2ቱ ፈጣን አትሌቶች የስዊዘርላንዷ ኦድሪ ዌሮ እና የኔዘርላንዷ ፌምኬ ብሮደርስ ቦል መሐል የሚኖረው ትንቅንቅ ይጠበቃል፡፡
የጽጌ ድጉማን መውጣት ተከትሎ ኢትዮጵያ በሰይዳ ጸሐዬ ብቻ የምትወከል ይኾናል፡፡ በዚህ የውድድር ዓመት በዶሃ፣ በሉዚያኔ እና ዙሪክ ላይ በርቀቱ የተወዳደረችው ሰይዳ በተለይም በዙሪክ ውድድር 4ኛ ደረጃን ይዛ ስታጠናቅቅ ጠንካራ ተፎካካሪ መኾኗን አሳይታለች፡፡
በሐናማርያም መስፍን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!



