በቅርቡ ዣቪ አሎንሶን ዋና አሠልጣኝ አድርጎ የሾመው የምዕራብ ለንደኑ የእግር ኳስ ቡድን ቸልሲ በክረምቱ የዝውውር መስኮት በንቃት እየተሳተፈ ይገኛል።
ሞርጋን ሮጀርስን እና ዳኒ ዌልቤክን ያስፈረመው እኔዲኹም ከጆርዳን ሄንደርሰንን ጋር የቃል ስምምነት ላይ የደረሰው ቸልሲ አሁን ደግሞ የ26 ዓመቱን የክርስቲያል ፓላስ ተከላካይ ማክሰንስ ላኮሪስን ማስፈረሙን ይፋ አድርጓል።
ቸልሲ ለዝውውሩ 52 ሚሊየን ፓውንድ ለክርስቲያል ፓላስ ይከፍላል። ተጫዋቹ በስታፎርድ ብሪጅ ለስድስት ዓመታት የሚያቆየውን የረጅም ጊዜ ውል መፈራረሙ ነው የተገለጸው።
ማክሰንስ የቀድሞ ክለቡ ክርስቲያል ፓላስ የኤፍኤ እና ኮንፈረንስ ሊግ ዋንጫዎችን እንዲያሸንፍ ከፍተኛ ሚና በመጫወቱ በትላልቅ ክለቦች ዕይታ ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል። በዣቪ አሎንሶ የጨዋታ ፍልስፍና የቸልሲን የመሃል ተከላከይ መስመር ክፍተት ለመሙላት ትልቅ አቅም ኾኖ እንደሚያገለግልም ይጠበቃል።
ተጫዋቹ እንደ ሊቨርፑል እና ባየርንሙኒክ ባሉ ታላላቅ የእግር ኳስ ቡድኖች በጥብቅ ሲፈለግ ነበር።
በአድኖ ማርቆስ



