ሪያል ማድሪድ ያን ዲዮማንዴን ለማስፈረም ከስምምነት ላይ ደርሷል።

0
93
የዓለም ኀያሉ የእግር ኳስ ቡድን ሪያል ማድሪድ አይቮሪኮስታዊውን ተጫዋች ያን ዲዮ ማንዴን ከአርቢ ሌፕዚንግ ለማስፈረም ሙሉ ስምምነት ላይ መድረሱ ተነግሯል።
ሪያል ማድሪድ ለተጫዋቹ ጥቅማጥቅምን ጨምሮ ከ 100 ሚሊዮን እስከ 120 ሚሊዮን ዮሮ ለሌፕዚንግ ለመክፈል ተስማምቷል። የዝውውር ዋጋው ዲዮማንዴን በታሪክ ውዱ አፍሪካዊ ተጫዋች እንደሚያደርገውም ተነግሯል።
የ19 ዓመቱ ያን ዲዮማንዴ በማድሪድ ቤት እ.ኤ.አ እስከ 2031 የሚያቆየውን የ5 ዓመት የረጅም ጊዜ ውል ይፈርማል። በዚህ ሳምንትም ወደ ማድሪድ ተጉዞ የሕክምና ምርመራውን እንደሚያደርግ ተዘግቧል።
ዝውውሩ በአሠልጣኝ ጆዜ ሞውሪንሆ ከፍተኛ ፍላጎት መመራቱ የተገለጸ ሲኾን በቪኒሽየስ ጁኒየር የክለቡ የወደፊት ቆይታ ላይ አዲስ ነገር ሊፈጥር እንደሚችል እየተነገረ ይገኛል።
ዘ አትሌቲክ ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው ቪኒሺየስ ጁንየር የቡድኑ ከፍተኛ ተከፋይ ለመኾን በመፈለጉ ሪያል ማድሪድ ያቀረበለትን የ 20 ሚሊዮን ዮሮ ዓመታዊ የተጣራ ደመወዝ ውድቅ አድርጓል። በዚህ የተነሳም ሲደረግ የነበረው የውል ማደስ ድርድር ተቋርጧል።
ቪኒሽየስን የክለቡ ከፍተኛ ተከፋይ በማድረግ ወደ ሰሜን ለንደን ለማስኮብለል ከፍተኛ ጥረት እያደረገ የሚገኘው አርሰናል ጥረቱን አሁንም አላቋረጠም። የዲዮማንዴ ዝውውር በመጠናቀቁ እና ቪኒሽየስ በማድሪድ ያለው ኮንትራት አንድ ዓመት ብቻ በመቅረቱ ሪያል ማድሪድ ተጫዋቹን በነፃ ላለማጣት ከ 160 ሚሊዮን ዩሮ በላይ በኾነ ዋጋ ሊሸጠው እንደሚችልም ኢኤስፒኤን ዘግቧል።
አሠልጣኝ ጆዜ ሞሪንሆ ከቪኒሺየስ ወኪሎች ጋር በነገው እለት ውይይት እንደሚያደርግም ተመላክቷል።
ዘጋቢ:- አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here