ከጎሎች ጀርባ የሚገኙ ቀዳሚ ተጫዋቾች !

0
111

 

ሊጠናቀቅ የአንድ ቀን ዕድሜ ብቻ በቀሩት 23ኛው የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ የውድድሩ ሻምፒዮን ሀገር የፊታችን እሑድ በአርጀንቲና እና ስፔን መካከል በሚደረግ የፍጻሜ ጨዋታ ይታወቃል፡፡

ሻምፒዮን ከሚኾነው ሀገር በተጨማሪ በኮከብ ግብ አግቢነት የወርቅ ጫማ አሸናፊ ለመኾን የሚደረገው ፉክክርም እስከመጨረሻው የሚዘልቅ ሲኾን እየተፎካከሩ ያሉት አራት ተጫዋቾች ደግሞ በፍጻሜ እና በደረጃ ጨዋታዎች ተሳታፊ ናቸው፡፡

የአርጀንቲናው ሊዮኔል ሜሲ እና የፈረንሳዩ ኬሊያን ምባፔ እኩል ስምንት ግቦች ይዘው ሲመሩ የእንግሊዞቹ ሀሪ ኬን እና ጁዲ ቤሊንግሀም በእኩል ስድስት ግቦች ይከተላሉ፡፡

በኮከብ ግብ አግቢነት ሕጉ መሠረት ሁለት ተጫዋቾች እኩል ግቦችን ይዘው ከጨረሱ ቀጣዩ መለያ ለተቆጠሩ ግቦች አመቻችተው ያቀበሉት መጠን ነው፡፡

በዚህ ረገድ አራት ኳሶችን ያመቻቸው ሊዮኔል ሜሲ ከምባፔ በአንድ ከፍ ብሎ ይመራል፡፡
ከዚሁ ለግብ የሚኾኑ ኳሶችን አመቻችቶ ከማቀበል ጋር በተያያዘ በቀዳሚነት እየመራ ያለው ግን የፈረንሳዩ አማካይ ማይክል ኦሊሴ ኾኖ እናገኜዋለን፡፡

ከዓለም ዋንጫው መጀመር በፊትም በባየር ሙኒክ ቤት ድንቅ የብቃት ጊዜን ያሳለፈው የ24 ዓመቱ ተጫዋች በ2025/26 የውድድር ዓመት ለጀርመኑ ክለብ 15 ግቦችን አስቆጥሮ 19 የተቆጠሩ ግቦችን አመቻችቶ አቀብሏል፡፡

በዚህ የዓለም ዋንጫ ደግሞ ፈረንሳይ እስካሁን ካስቆጠረቻቸው 16 ግቦች ውስጥ አምስቱን በማመቻቸት ቀዳሚው ተጫዋች ኾኗል፡፡

በኦሊሴ ከተመቻቹት ኳሶች ውስጥ ሦሥቱን ኬሊያን ምባፔ ከሴኔጋል፣ ኢራቅ እና ስዊድን ላይ ሲያስቆጥር ቀሪዎቹን የእርሱን ድንቅ ኳሶች ኦስማን ዴምቤሌ ኢራቅ ላይ፣ ብራድሊ ባርኮላ ስዊድን ላይ በአግባቡ ተጠቅመውባቸዋል፡፡

ከማይክል ኦሊሴ በመቀጠል ሊዮኔል ሜሲን ጨምሮ የሞሮኮው ብራሂም ዲያዝ፣ የኖርዌዩ ማርቲን ኦዲጋርድ እና የብራዚሉ ብሩኖ ጉማሬይሽ እኩል አራት የግብ ኳሶችን በማመቻቸት ይከተላሉ፡፡

ማይክል ኦሊሴ ሀገሩ ፈረንሳይ በደረጃ ጨዋታ ከእንግሊዝ ጋር ተጋጣሚ በመኾኗ በአንድ የዓለም ዋንጫ ውድድር በርካታ ለግብ የሚኾኑ ኳሶችን በማመቻቸት ረገድ ክብረ ወሰኑን የመስበር ዕድል አለው፡፡

ከዚህ በፊት ከብረ ወሰኑ የተያዘው እ.አ.አ በ1970 የዓለም ዋንጫ ስድስት የግብ ዕድሎችን በፈጠረው የእግር ኳሱ ንጉስ ብራዚላዊው ፔሌ መኾኑን የያሁ ስፖርትስ መረጃ ያመለክታል፡፡

#አሚኮ #ስፖርት

#ባሕር_ዳር_ሐምሌ11_2018_ዓ_ም

በኃይሌ አበራ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here