ኖርዌይ ረጅም የባሕር ዳርቻ ያላት ሀገር ስለኾነች ሕዝቦቿ ለብዙ መቶ ዓመታት በባሕር ጉዞ፤ በዓሳ ማጥመድ እና በመርከብ ንግድ ይታወቃሉ፡፡ በተለይ የጥንቱ ቫይኪንጎች (Vikings) በረጅም መርከቦቻቸው ውቅያኖሶችን እየተሻገሩ የተጓዙ እና የተስፋፉ ነበሩ፡፡
ኖርዌይ በ2026ቱ የዓለም ዋንጫ መሳተፍ የቻለችው ከ28 ዓመታት በኋላ ነው፡፡ አሁን ላይ ግን በሩብ ፍጻሜው ከእንግሊዝ ጋር ተፋላሚ ናት፡፡
የኖርዌይ ብሔራዊ ቡድን ደጋፊዎች በ23ኛው የዓለም ዋንጫ የቀዘፋ ትርዒታቸው የዓለምን ሕዝብ ትኩረት በመሳብ ላይ ይገኛሉ፡፡ ደጋፊዎቹ በስታዲየም ውስጥ የቫይኪንግ መርከብን የሚያስታውሱ የመቅዘፍ እንቅስቃሴዎችን ወይም የጀልባ መቅዘፍን የሚመስሉ ዘፈኖች እና እንቅስቃሴዎችን ያደርጋሉ፡፡
የኖርዌይ ደጋፊዎች የቀዘፋ ትርዒት የብሔራዊ ቡድኑ ምልክት ሳይኾን የኖርዌይን የባሕር ታሪክ እና የቫይኪንግ ቅርስ ለማክበር የሚደረግ የደጋፊዎች ባሕል ነው፡፡
የኖርዌይ ደጋፊዎቹ ብቻ ሳይኾኑ ተጨዋቾቹም ከድል በኋላ በስታዲየሙ መሀል ተቀምጠው ከደጋፊዎቻቸው ጋር በጋራ እየቀዘፉ መርከባቸውን ወደ ፊት በማስኬድ ላይ ይገኛሉ፡፡
የአርሰናሉ አምበል ማርቲን ኦዲጋርድ እና የማንቸስተር ሲቲው ፊታውራሪ ኸርሊንግ ብራውንት ሃላንድ ደግሞ የመርከቧ ካፒቴን ኾነው ቀዘፋውን ይመሩታል፡፡
ኖርዌይ በጥሎ ማለፉ የአምስት ጊዜ ሻምፒዮናዋን ብራዚልን 2 ለ 1 አሸንፋ ከውድድሩ ስታሰናብታት ሁለቱንም ግቦች ያስቆጠረው አጥቂዋ ሃላንድ ነው፡፡ ሃላንድ በውድድሩ ሰባት ግቦችን በማስቆጠር የኮከብ ግብ አስቆጣሪነቱንም ከሜሲ፣ ምባፔ እና ሃሪ ኬን ጋር በመፎካከር ላይ ይገኛል፡፡
ኖርዌይ የዓለም ዋንጫውን አንድ ጊዜ ብቻ ካሳካችው ከእንግሊዝ ጋር የምታደርገው ፍልሚያ በእጅጉ ተጠባቂ ኾኗል፡፡ በውድድሩ ሰባት ግቦችን ያስቆጠረው ሃላንድ እና ስድስት ግቦችን ያስቆጠረው ሃሪ ኬን ለየሀገሮቻቸው የሚያደርጉት የግብ ማስቆጠር ፉክክርም ሌላው አጓጊ ጉዳይ ነው፡፡
ቀዛፊዎቹ ኖርዌጂያኑ ስለምን በጋራ እንደሚቀዝፉ ሲጠየቁ “በጋራ መርከባችንን ካሰብንበት ቦታ ለማድረስ” የሚል ምላሽ መስጠታቸውን የቢቢሲ ስፖርት መረጃ ያመለክታል፡፡
የኖርዌይ ተጨዋቾች እና ደጋፊዎቻቸው በጋራ የሚቀዝፏት መርከባቸው በ23ኛው የዓለም ዋንጫ ማረፊያ ወደቧ የት እንደሚኾን በቀጣይ የምናየው ይኾናል፡፡
#አሚኮ_ዜና #ስፖርት #ዓለምዋንጫ #ባሕር_ዳር #ሐምሌ4_2018_ዓ_ም
በእሱባለው ይርጋ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!



