ሀሪ ኬን ከሀላንድ፤ ሜሲ ከዣካ የምሽቱ ተጠባቂ ፍጥጫዎች !

0
149

 

በ23ኛው የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ውድድር ፈረንሳይ እና ስፔን ግማሽ ፍጻሜውን መቀላቀላቸውን አረጋግጠዋል፡፡ ቀሪዎቹን ሀገራት ለመለየት የሚደረጉት ሁለት የሩብ ፍጻሜ ጨዋታዎች ዛሬ ምሽት ይካሄዳሉ፡፡

ከእነዚህ መካከል እንግሊዝ እና ኖርዌይ ምሽት 6፡00 ላይ በሚያሚ ስታዲየም ይገናኛሉ፡፡

ሁለቱ ሀገራት በእስከዛሬ ታሪካቸው 12 ጊዜ ተገናኝተዋል፡፡ እንግሊዝ ሰባት ኖርዌይ ሁለት ጊዜ ሲያሸንፉ በቀሪ ሦስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል፡፡

እንግሊዝ ከ60 ዓመታት በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ የዓለም ዋንጫ ሻምፒዮን የመኾን ጉዞዋን ለማመቻቸት ዛሬ ምሽት ወደ ሜዳ ትገባለች፡፡ የኖርዌይ ከፍተኛ የዓለም ዋንጫ ጉዞ ግን በ1998ቱ መድረክ 16ቱ ውስጥ የደረሰችበት ነው፡፡
በምሽቱ ጨዋታ የሁለቱ ቀንደኛ የግብ አዳኞቹ ሀሪ ኬን እና ኸርሊንግ ሀላንድ ፍጥጫ ይጠበቃል፡፡ በዚህ የዓለም ዋንጫ ሀላንድ 7፣ ኬን 6 ግቦችን በማስቆጠር በወርቅ ጫማ አሸናፊነት ፉክክሩ ውስጥ ይገኛሉ፡፡

ሌሊት 10፡00 ላይ በካንሳስ ሲቲ ስታዲየም በሚካሄደው የመጨረሻው የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ አርጀንቲና ከስዊዘርላንድ ይገናኛሉ፡፡
በአርጀንቲና በኩል በምድብ መርሐ ግብር ሦስቱንም ጨዋታዎች አሸንፋ በበላይነት ብታጠናቅቅም በሁለቱ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎቿ ግን በአፍሪካዊያኑ ኬፕ ቨርዲና ግብጽ በእጅጉ ተፈትና ነው ለሩብ ፍጻሜ የደረሰችው፡፡

ያልተጠበቀ ድንቅ አቋም እያሳየች ያለችው ስዊዘርላንድ በበኩሏ ከምድቧ በሰባት ነጥብ በመሪነት አጠናቅቃ፣ 32ቱ ውስጥ አልጀሪያን በጨዋታ፣ 16ቱ ውስጥ ደግሞ ኮሎምቢያን በመለያ ፍጹም ቅጣት ምት አሸንፋ ለሩብ ፍጻሜው በቅታለች፡፡

በምሽቱ ጨዋታ በግራኔት ዣካ ድንቅ ብቃት በአግባቡ የተደራጀው የስዊዘርላንድ የአማካይ ክፍል በሊዮኔል ሜሲ የሚመራውን የአርጀንቲና የማጥቃት እንቅስቃሴ ለማቆም የሚያደርጉት ትንቅንቅ ይጠበቃል፡፡

ጨዋታው ለ2022ቱ ውድድር ሻምፒዮኗ አርጀንቲና ከ64 ዓመት በፊት ብራዚል ያሳካችውን የተከታታይ የዓለም ዋንጫ ሻምፒየናነት ገድል ለመድገም ጉዞዋን የምታመቻችበት ይኾናል፡፡

በስዊዘርላንድ በኩል በዓለም ዋንጫ መድረክ ሩብ ፍጻሜ ላይ ስትገኝ ከ72 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ መኾኑን የሱፐር ስፖርት እና ኤ ኤፍ ፒ ዘገባዎች አመልክተዋል፡፡

#አሚኮ_ዜና #ስፖርት #ዓለምዋንጫ
#ባሕር_ዳር #ሐምሌ4_2018_ዓ_ም

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here