የምባፔ እና የሀኪሚ ፍልሚያ ዛሬ ይጠበቃል !

0
35
በሜዳ ላይ ያላቸው ጥንካሬ፤ ፈጣን አጨዋወት፤ የዕድሜ እኩያ መኾን እና የቡድናቸው አምበልነት ያመሳስላቸዋል። የልብ ጓደኛ የኾኑት እና ለብሔራዊ ቡድኖቻቸው መተማመኛ ቁልፍ የኾኑት ኬልያን ምባፔ እና አሽራፍ ሀኪሚ ምሽቱን ተቃራኒ ኾነው ለሀገራቸው ክብር ሊፋለሙ ተዘጋጅተዋል።
ሁለቱ ኮከቦች በፈረንሳዩ ፒኤስጂ ክለብ በጋራ ባሳለፏቸው ጣፋጭ የስኬት ዓመታት ግብ ሲያስቆጥሩ የሚያሳዩት “የፔንግዊን ዳንስ” የደስታ አገላለጽ የቅርብ ወዳጅነታቸው መገለጫ ነበር።
ሀኪሚ በ2021 ከኢንተርሚላን ፒኤስጂን ሲቀላቀል ፈጥኖ ቋንቋውን እንዲረዳ ምባፔ ትልቅ እገዛ አድርጎለታል። ከሜዳ ውጭም የእረፍት ጊዜያቸውን በተለያዩ ሀገራት በጋራ የሚያሳልፉት እነዚህ ተጫዋቾች በስፖርቱ ዓለም ደስ የሚል የጓደኝነት ታሪክ አላቸው።
የሁለቱ ኮከቦች ልዩ ወዳጅነት የዓለምን ትኩረት የሳበው በ2022 የኳታሩ የዓለም ዋንጫ ግማሽ ፍጻሜ ላይ ፈረንሳይ እና ሞሮኮ ሲገናኙ ነበር።
በወቅቱ ምባፔ በፈረንሳይ በኩል በግራ ክንፍ ሲያጠቃ ሀኪሚ ደግሞ በሞሮኮ በቀኝ ተከላካይነት እሱን የመቆለፍ ከባድ ኀላፊነት ነበረበት።
ጨዋታው በፈረንሳይ 2 ለ 0 አሸናፊነት ከተጠናቀቀ በኋላ ምባፔ ወዲያውኑ ወደ ሀኪሚ በመሄድ ያጽናናው ሲኾን በስታዲየሙ መተላለፊያ ኮሪደር ላይ መሬት ላይ ተቀምጠው ሲያወሩ የሚያሳየው ምስል በዓለም ዙሪያ ማነጋገሩ ይታወሳል።
የታሪክ አጋጣሚ ኾኖ ዛሬ ምሽትም ሁለቱ የልብ ወዳጆች በድጋሚ ይፋለማሉ። በኳታሩ የዓለም ዋንጫ ምንም እንኳን ሞሮኮ ብትሸነፍም፣ 61 በመቶ የጨዋታ ብልጫ ወስዳ ጠንካራ ተፎካካሪ መኾኗን አስመስክራ ነበር።
ዛሬ ምሽት “የአትላስ አንበሶቹ” የደረሰባቸውን የኳታሩን ሽንፈት ለመመለስ ወደ ሜዳ የሚገቡ ሲኽን፤ ፈረንሳይ በበኩሏ ለሻምፒዮንነት በሚጠበቀው አዲስ ትውልዷ ሌላ ታሪክ ለመጻፍ ትፋለማለች።
የፈረንሳዩ አሠልጣኝ ዲዲየር ዴሾ የሞሮኮን ፈጣን ማጥቃት እና የመከላከል አደረጃጀት በማድነቅ አጨዋወታቸው አደገኛ በመኾኑ ተጫዋቾቻቸው ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ መክረዋል።
በኳታሩ ጨዋታ በሄርናንዴዝ እና በኮሎ ሙዋኒ ግቦች ለፍጻሜ የማለፍ ተስፋዋ የመከነው ሞሮኮ ዛሬ ምሽት የመልስ ምት በመስጠት ሀሳቧን ታሳካ ይኾን ወይንስ ለተከታታይ ጊዜ በፈረንሳይ የበላይነት ይወሰድባታል? የምሽቱ 5:00 ጨዋታ ምላሽ አለው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here