ባሕር ዳር: ሰኔ 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢራን ብሔራዊ ቡድን በሎስ አንጀለስ ሶፋይ ስታዲየም ከቤልጂየም ጋር 0 ለ 0 በሆነ አቻ ውጤት ከተለያየ በኋላ በልብስ መቀየሪያ ክፍል ውስጥ የተውት በእጅ የተጻፈ ልብ የሚነካ መልዕክት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የዜና ሽፋን አግኝቷል።
ሎስ አንጀለስ «ቲም መሊ» በሚል ቅጽል ስም የሚታወቀው የኢራን ወንዶች ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን በ2026 የፊፋ ዓለም ዋንጫ በሜዳ ላይ በሚያሳየው ጨዋታ ብቻ ሳይኾን ከሜዳ ውጭ ባለው ስፖርታዊ ጨዋነቱ የዓለምን ትኩረት በድጋሚ ስቧል።
ቡድኑ እሁድ ዕለት በሎስ አንጀለስ ከጠንካራዋ ቤልጂየም ጋር ያደረገውን ጨዋታ 0 ለ 0 በኾነ አቻ ውጤት ካጠናቀቀ በኋላ ከስታዲየሙ በፍጥነት ከመውጣቱ በፊት በልብስ መቀየሪያ ክፍሉ ውስጥ በእጅ የተጻፈ ልብ የሚነካ ደብዳቤ አስቀምጦ ወጥቷል።
የሎስ አንጀለስን ከተማ መስተንግዶ ያደነቀው እና የኢራን ዲያስፖራዎችን ያላሰለሰ ድጋፍ ያከበረው ይህ መልዕክት በአጭር ጊዜ ውስጥ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የስፖርት ዲፕሎማሲ ትልቅ ምልክት ኾኖ ታይቷል።
ኢራኖች የዘንድሮው የ2026 የዓለም ዋንጫ ጉዟቸው ከፖለቲካዊ እና ከሎጅስቲክስ አንጻር እጅግ አድካሚ ኾኖባቸዋል። በጂኦፖለቲካዊ ውጥረቶች እና በጥብቅ የጉዞ ገደቦች ምክንያት ቡድኑ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የልምምድ ካምፕ እንዲያደርግ ባለመፈቀዱ ካምፑን በቲዋና (ሜክሲኮ) ለመመስረት ተገዷል። በዚህም ምክንያት ቡድኑ እያንዳንዱ ጨዋታ ከተጠናቀቀ በኋላ ወዲያውኑ ወደ ሜክሲኮ በአውሮፕላን እንዲመለስ በመደረጉ በጨዋታው ድካም ላይ ተጨማሪ አካላዊ ጫና ፈጥሮባቸዋል።
ከካሊፎርኒያ ተነስተው ወደ ሜክሲኮ ከመብረራቸው በፊት የቡድኑ አባላት የሚከተለውን መልዕክት አስፍረዋል፦
በካሊፎርኒያ በሚኖሩ በርካታ የኢራን ዲያስፖራዎች ፊት የተደረጉት እነዚህ ሁለት ጨዋታዎች በደጋፊዎች እና በቡድኑ መካከል ያለውን ጥልቅ ትስስር ያሳዩ ነበሩ።
ኢራን በሁለት ጨዋታዎች 2 ነጥብ በመያዝ፣ ታሪካዊ የኾነውን የምድብ ማጣሪያ አልፎ ወደ ጥሎ ማለፍ ዙር ለመጀመሪያ ጊዜ ለመግባት የመጨረሻ የምድብ ጨዋታዋን በሲያትል ከግብፅ ጋር ታደርጋለች።
ኢራን በዓለም ዋንጫ ሰባት ጊዜ ተሳትፋለች፤ ወደ ጥሎ ማለፍ ግን አልፋ የማታውቅ ሀገር ናት።
ዘንድሮስ ወደ ሚቀጥለው ዙር ታልፋለች ብለው ያስባሉ?
በሰለሞን ጥበቡ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



