🌍🏆 የዓለም ዋንጫ አይረሴ ክስተቶች!

0
52

 

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በእግር ኳስ ታሪክ ውስጥ የማይረሱ እና ትውልድ ተሻጋሪ የኾኑ የዓለም ዋንጫ ገጠመኞች እና ክስተቶች መኖራቸው አይቀሬ ነገር ነው።

ከእነዚህ መካከል ቀድሞ የሚታወሰው ሜክሲኮ ላይ እ.አ.አ 1986 ላይ በተካሄደው ጨዋታ የዲያጎ ማራዶና ድንቅ እና አወዛጋቢ ክስተት ይጠቀሳል። የፊፋ መረጃ እንደሚያሳየው በአርጀንቲና እና እንግሊዝ ጨዋታ ላይ ማራዶና በእጁ በመንካት ያስቆጠራት ጎል እግር ኳስን ካናወጡ ክስተቶች ቀዳሚ አድርጓታል።

ማራዶና ከጨዋታው በኋላ “ጎሏ ጥቂት በማራዶና ራስ፣ ጥቂት ደግሞ በእግዚአብሔር እጅ የተቆጠረች ናት” ነበር ያለው። ከዚህች ጎል ከአራት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ስድስት የእንግሊዝ ተጫዋቾችን አታልሎ የክፍለ ዘመኑን ምርጥ ጎል ማስቆጠሩ ሲታወስ ይኖራል። ይህም አይረሴ ክስተቱን ይበልጥ አጉልቶታል።

በሌላ በኩል ጀርመን ላይ የተካሄደው የ2006ቱ የዓለም ዋንጫ ፍጻሜም ፈረንሳይ ከኢጣሊያ ጋር ባደረጉት ጨዋታ የዓለም እግር ኳስ ኮከቡ ዚነዲን ዚዳን ያሳየው ያልተጠበቀ ባህሪ ሌላኛው ታሪካዊ ገጠመኝ ነው።

የጣሊያኑ ተከላካይ ማርኮ ማቴራዚ በሰደበው ስድብ የተበሳጨው ዚነዲን ዚዳን በፍጻሜው ጨዋታ ተጨማሪ ሰዓት ላይ ማቴራዚን በደረት እና በራሱ በመምታቱ በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል። ይህ ክስተት የዚነዲን ዚዳንን የመጨረሻ የፕሮፌሽናል ጨዋታ በሃዘን እንዲደመድም አድርጎታል።

የ1990 የዓለም ዋንጫ ጨዋታ ደግሞ የ38 ዓመቱ የካሜሩን አጥቂ ሮጀር ሚላ ያስመዘገበው ታሪክ ለአፍሪካ ትልቅ ኩራት ነበር። ጎል ባስቆጠረ ቁጥር ወደ ማዕዘን እየሄደ ባንዲራ ይዞ የሚያሳየው ውብ የወገብ ዳንስ የዓለም ዋንጫን ደስታ የቀየረ እና እስከ ዛሬ ድረስ በተጫዋቾች ዘንድ የሚታወስ አይረሴ ገጠመኝ ኾኖ ቀርቷል። ካሜሮንም የመጀመሪያዋ ሩብ ፍጻሜ የደረሰች የአፍሪካ ሀገር ኾና ነበር።

ቢቢሲ እና ስካይ ስፖርት እንዳገኘነው መረጃ በእግር ኳስ ታሪክ እጅግ አስደንጋጭ ከኾኑት ጨዋታዎች አንዱ ደግሞ በ2014 ዓ.ም በብራዚል አስተናጋጅነት የተደረገው የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ነው። ጀርመን የዓለም እግር ኳስ ነገሥታት የኾኑትን ብራዚላውያንን በገዛ ሜዳቸው እና በደጋፊዎቻቸው ፊት 7 ለ 1 ያሸነፈችበት መንገድ ሙሉ ስታዲየሙን በዕንባ ያጠለቀ እና መላውን ዓለም ያስገረመ ክስተት ነበር።

በኳታር የተካሄደው የ2022ቱ የዓለም ዋንጫ ፍጻሜም በታሪክ እጅግ አስደሳች እና ውጥረት የነገሰበት ጨዋታ ነበር። አርጀንቲና እና ፈረንሳይ 3 ለ 3 ተለያይተው በመለያ ምት አርጀንቲና ስታሸንፍ ሊዮኔል ሜሲ ያላገኘውን ብቸኛ ትልቅ ዋንጫ በማንሳት ታሪክ ሰርቷል።

ሜሲ በባሕላዊው የኳታር ልብስ ተውቦ ዋንጫውን ወደ ሰማይ ያነሳበት ምስል የማይረሳ የታሪክ አካል ኾኗል።

የዘንድሮው የዓለም ዋንጫስ ምን አይረሴ ገጠመኝ ይዞ ይመጣል? ምንስ ክስተት ይታይበት ይኾን? አብረን እናየዋለን!

ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here