ባሕር ዳር: ሰኔ 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ጀርመናዊው ሚሮስላቭ ክሎስ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2002 እስከ 2014 ባሉት የዓለም ዋንጫዎች በጀርመን መለያ 16 ግቦችን ከመረብ አሳርፏል፡፡ ይኼው የግብ መጠንም እስካሁኑ የዓለም ዋንጫ ድረስ ክብረ ወሰን ኾኖ ተመዝግቧል፡፡
ኳታር ባዘጋጀችው የ2022 የዓለም ዋንጫ የተመዘገቡት አራት ቀይ ካርዶች ብቻ ናቸው፡፡ በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ግን በመክፈቻው የሜክሲኮ እና የደቡብ አፍሪካ ጨዋታ ብቻ ከወዲሁ ሦስት የቀይ ካርዶች ተመዘዋል፡፡ በ2026ቱ የዓለም ዋንጫ ከሚሻሻሉት ክብረ ወሰኖች ውስጥ የሚሮስላቭ ክሎስ 16 ግቦችስ ይኖሩበት ይኾን?
ብራዚላዊው ሮናልዶ ናዛሪዮ እ.አ.አ ከ1998 እስከ 2006 ባሉት የዓለም ዋንጫዎች 15 ግቦችን በማስቆጠር ከክሎስ ቀጥሎ ሁለተኛው የዓለም ዋንጫ ብዙ ግብ አስቆጣሪ በሚል ስሙን አስመዝግቧል፡፡
ሌላኛው ጀርመናዊ የግብ አዳኝ ገርድ ሙለር ደግሞ ከ1970 እስከ 1974 ባሉት የዓለም ዋንጫ ሁለት ጨዋታዎች 14 ግቦችን ከመረብ ላይ አሳርፏል፡፡
ፈረንሳዊው ጀስት ፎንቴን በዓለም ዋንጫ ጨዋታዎች ያስቆጠራቸው ግቦች 13 ሲኾኑ እነዚህ 13 ግቦች የተቆጠሩት ግን በ1958 በተደረገው የዓለም ዋንጫ ላይ ብቻ መኾኑ የፎንቴንን ግቦች ልዩ ያደርጓቸዋል፡፡
አርጀንቲናዊው ሊዮኔል ሜሲ እ.አ.አ ከ2006 እስከ 2022 ለአርጀንቲና ብሔራዊ ቡድን በዓለም ዋንጫ 13 ግቦችን ያስቆጠረ ሲኾን አሜሪካ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ ባዘጋጁት የ2026 የዓለም ዋንጫ ላይም እየተሳተፈ በመኾኑ የሚሮስላቭ ክሎስን ክብረ ወሰን ለመጋራት ወይም ለማሻሻል ዕድሉ ካላቸው ተጨዋቾች አንዱ ነው፡፡
ታዋቂው ብራዚላዊ የእግር ኳስ ሰው ፔሌም ከ1958 እስከ 1970 ባሉት የዓለም ዋንጫዎች ለሀገሩ ብራዚል 12 ግቦችን አስቆጥሯል፡፡
ፈረንሳዊው የሪያል ማድሪዱ አጥቂ ኪሊያን ምባፔ በሁለት የዓለም ዋንጫዎች ከ2018 እስከ 2022 ባደረጋቸው ጨዋታዎች 12 ግቦችን ከመረብ ላይ አሳርፏል፡፡ ምባፔ ዘንድሮም የፈረንሳይን የፊት መሥመር የሚመራው እሱ ከመኾኑ ጋር ተያይዞ የሚሮስላቭ ክሎስን የ16 ግቦች ክብረ ወሰን ለመጋራት ወይም ለማሻሻል ተስፋ ከተጣለባቸው ተጨዋቾች አንዱ ነው፡፡
ከፊፋ ድረ ገጽ ባገኘነው መረጃ መሠረት በ1958 የዓለም ዋንጫ በፈረንሳዊው ጀስት ፎንቴን 13 ግቦች ተይዞ የነበረው ክብረ ወሰን በ1974 በገርድ ሙለር 14 ግቦች፣ በ2006 በሮናልዶ ናዛሪዮ 15 ግቦች የተሻሻሉ ሲኾን ሚሮስላቭ ክሎስ በ2014 ያስመዘገበው የ16 ግቦች ክብረ ወሰን ግን እስካሁንም ድረስ የዓለም ዋንጫ ክብረ ወሰን ኾኖ እንደቀጠለ ነው፡፡
በዓለም ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታዎች አራት ግቦችን በማስቆጠር የራሱን ክብረ ወሰን የጻፈው ኪሊያን ምባፔ (በ2018 አንድ ግብ እና በ2022 ሦስት ግቦች) በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ አራት እና ከዚያ በላይ ግቦችን የሚያስቆጥር ከኾነ ባለ ክብረ ወሰኑ እሱ መኾን ይችላል፡፡
አርጀንቲናዊው ሊዮኔል ሜሲም በ2026 በሚያደርገው የመጨረሻው የዓለም ዋንጫ ተሳትፎው ሦስት እና ከዚያ በላይ ግቦችን የሚያስቆጥር ከኾነ ስሙን በክብር መዝገብ ላይ ማስፈር ይችላል፡፡
የዓለም ዋንጫው የ16 ግብ ክብረ ወሰን በማን ይሻሻል ይኾን?
በእሱባለው ይርጋ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



