የአውሮፓ እግር ኳስ ክለቦች በቀጣይ የዝውውር መስኮት ላይ ምን ያስመለክቱን ይኾን ?

0
25

 

ባሕር ዳር: ግንቦት 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአውሮፓ እግር ኳስ የክረምት የዝውውር መስኮት ሊከፈት ጥቂት ጊዜ በቀሩት በአሁኑ ወቅት ታላላቅ ክለቦች ሥብሥባቸውን ለማጠናከር እና ተጫዋቾችን ለመሸጥ ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረጉ ይገኛሉ።

አርሰናል የ29 ዓመቱን ብራዚላዊ አጥቂ ገብርኤል ጂሰስን በዚህ ክረምት አሳልፎ ለመስጠት እስከ 20 ሚሊዮን ፓውንድ እየጠየቀ ይገኛል።

በአንጻሩ አርሰናል የ23 ዓመቱን የአስቶን ቪላ እና የእንግሊዝ አማካኝ ሞርጋን ሮጀርስን ለማስፈረም ሰፊ እና ዝርዝር ዝግጅቶችን አድርጓል።

የማንቸስተር ሲቲው የ22 ዓመት ብራዚላዊ የክንፍ ተጫዋች ሳቪንሆ በቶተንሃም በኩል ፍላጎት በመኖሩ ምክንያት ሲቲን የመልቀቅ ዕድል እንዳለው ፍንጭ ሰጥቷል።

ማንቸስተር ሲቲ ከአሠልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ መነሳት በኋላ የሚኖረውን አዲስ ምዕራፍ ለመጀመር የኖቲንግሃም ፎረስት እና የእንግሊዝ አማካኝ የኾውን የ23 ዓመቱን ኤሊዮት አንደርሰንን ማስፈረም ዋነኛ ቅድሚያ የሚሰጠው ሥራ አድርጎታል።

ሲቲዎች ቼልሲን መልቀቅ ይፈልጋል የተባለውን የ25 ዓመቱን የአርጀንቲና አማካኝ ኤንዞ ፈርናንዴዝን የማስፈረም ምንም ዓይነት ፍላጎት የሌላቸው መኾኑ ተረጋግጧል።

ሊቨርፑል የ33 ዓመቱን ብራዚላዊ ግብ ጠባቂ አሊሰን ቤከርን ለአንድ ተጨማሪ የውድድር ዓመት በክለቡ ማቆየት ይፈልጋል። ይህም ተጫዋቹ ወደ ጁቬንቱስ ሊያደርገው የነበረውን ዝውውር ጥርጣሬ ላይ ጥሎታል።

የሊቨርፑል እና የኢንተር ሚላን ክለብ ኀላፊዎች የ25 ዓመቱ እንግሊዛዊ አማካኝ ከርቲስ ጆንስ ወደ ጣሊያን ሊዘዋወር በሚችልበት ሁኔታ ላይ ተገናኝተው ተወያይተዋል።

አር ቢ ሌፕዚሽ ለቀጣዩ የሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ማለፉን ተከትሎ፣ የሊቨርፑል ኢላማ የኾነው የ19 ዓመቱ የኮትዲቯር የክንፍ ተጫዋች ያን ዲዮማንዴ በዚህ ክረምት ከክለቡ እንደማይነቃነቅ አስታውቋል።

የጀርመኑ ክለብ ባየር ሌቨርኩሰን ከቦርንማውዝ የሚለቀቀውን አንዶኒ ኢራኦላን አዲሱ አሠልጣኛቸው አድርገው ለመቅጠር የማሳመን ሥራ ላይ ይገኛሉ።

ቢቢሲ በጭምጭምታ አምዱ እንዳስነበበው ኮንትራቱ አልቆ ነጻ ወኪል ለመኾን የተቃረበው የሴልታቪጎ እና የስፔን ተከላካይ ኦስካር ሚንጌዛ ወደ እንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ መዘዋወር ይፈልጋል። ተጫዋቹን አስቶን ቪላ እና ኒውካስትል በቅርብ እየተከታተሉት ይገኛሉ።

#አሚኮ_ዜና #ስፖርት_ዝውውር_እግር_ኳስ

በምስጋናው ብርሃኔ

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here