ባሕር ዳር: ግንቦት 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ሌዊ እንወድሃለን፤ ቤታችን ቤትህ፤ ታሪካችን ታሪክህ፣ ስኬታችን ስኬትህ፤ ደስታችን ደስታህ፣ ትዝታችንም ትዝታህ ነው ብለውታል።
አንድ ጊዜ የእኛ ኾነሃልና ሁልጊዜ የእኛ ነህ። ባርሴሎና ሁልጊዜ የአንተ ቤት ነው፤ ሌዊ ትናፍቀናለህ እያሉ ሳግ በሚተናነቀው አንደበታቸው ዘመሩለት።
እንባቸውን እያፈሰሱ ሸኙት፤ ትዝታውን ትዝታቸው፤ ታሪኩን ታሪካቸው አድርገው ሊያስቡት ተሰናበቱት። እነዚያ የደስታ ጊዜያት አልፈዋል። በዚያ ያማረ ስታዲየም ውስጥ የሚኖርበት ጊዜ አልቋልና እርሱም በእንባ ተሰናበታቸው።
እርሱ ዘመናዊ እግር ኳስ ካያቸው ምርጥ ዘጠኝ ቁጥር አጥቂዎች መካከል አንደኛው ነው። ግብ ለማስቆጠር የተካነ፤ ኳስን አሳምሮ የመጫወት ጥበብ የተቸረው፣ በታላላቅ ጨዋታዎች፣ በአስደናቂ ስታዲዬሞች በችሎታው የቦረቀ ታላቅ ተጫዋች ነው።
ብዙ ክለቦች እንዲኖራቸው የተመኙት፤ ተከላካዮች የሚጨነቁለት፤ ግብ ጠባቂዎች የሚፈሩት፤ የሚያሰለጥኑ አሠልጣኞች አብዝተው የሚወዱት፤ የተቃራኒ ክለብ አሠልጣኞች ደግሞ የሚሰጉት የዘመኑ
ድንቅ አጥቂ ነው ሮበርት ሌዋንዶውስኪ።
የጀርመን ስታዲየሞችን ፈንጭቶባቸዋል፤ ከስኬት ላይ ስኬት ደርቦባቸዋል፤ የስፔን ስታዲዬሞችን ቦርቆባቸዋል፤ እንደ አሻው ግብ አስቆጥሮባቸዋል። በጀርመን ቦርሲያ ዶርትመንድ ሲግናም ኢዱና ፓርክ የጎላው ስሙ፤ በባየርን ሙኒክ አልያዝን አሬና ገናና ኾኗል፤ ከዚያም ተሻግሮ በባርሴሎና ታሪክ ጽፏል።
የጀመርን ቦንደስሊጋ በድረ ገጹ ስለ ሮበርት ሌዋንዶውስኪ በጻፈው የኋላ ታሪክ እርሱ ከቀጫጫነት ተነስቶ በዓለም እግር ኳስ ኮኮብ የኾነ ተጫዋች ነው ይላል። ፖላንዳዊው ሮበርት ሌዋንዶውስኪ ያደገው በስፖርተኛ ቤተሰብ ውስጥ ነው።
እናቱ ለፖላንድ የቮሊቦል ስፖርት ይጫወቱ ነበር። አባቱ ደግሞ እግር ኳስን ይጫወት ነበር። ሁለቱም የአካል ብቃት ማሠልጠኛ መምህራን ኾነው ሠርተዋል። ወላጆቹ የልጃቸውን ተሰጥኦ እና የወደፊት መዳረሻ የተረዱት ገና በልጅነቱ ነው።
ይህ አስደናቂ ተጫዋች ወደ ስኬት ማማ ከመውጣቱ አስቀድሞ በርካታ ውጣ ውረዶችን አሳልፏል። የልጅነት ተሰጥኦውን አይተው ይንከባከቡት የነበሩት አባቱ ከስኬት ማማ ላይ ሳይደርስ ነበር ሕይወታቸው ያለፈው። ገና በታዳጊነቱ በቫርሶቪያ (Varsovia) ክለብ ሲጫወት ለረጅም ሰዓታት እያሽከረከሩ እርሱን በማመላለስ ሕልሙን እንዲኖር ሲያደርጉት የነበሩት አባቱ መሞት ለእርሱ ትልቅ ፈተና ነበር።
እርሱ ግን በፈተና አልተበገረም፤ አባቱ የጣሉበትን ተስፋ እውን ያደርግ ዘንድ በርትቶ ሠራ። “የአባቴ ትውስታ አሁንም ያበረታኛል፤ ተጨማሪ ልምምዶችን ሥሠራ ለራሴ “ይህንን የማደርገው ለእርሱ ነው” እላለሁ፤ ይህም ጥሩ መነሳሳትን ይሰጠኛል” ይላል። ፈተናዎች ግን ይደራረቡበት ነበር።
ሮበርት ሌዋንዶውስኪ ከአባቱ መሞት በኋላ የሀገሩን ክለብ ሌጊያ ዋርሶን ተቀላቀለ። በዚያ ቆይታው የጉልበት ጉዳት ገጠመው። ይህ ደግሞ ለእግር ኳስ ሕይወቱ ተጨማሪ ፈተና ይዞበት መጣ። ክለቡ ሮበርት ሌዋንዶውስኪን አሰናበተው። ያን ጊዜ 17 ዓመቱ ነበር።
“በሕይወቴ ካሳለፍኳቸው በጣም መጥፎ ቀናት አንዱ ነበር፤ ያን ጊዜ የእግር ኳስ ሕይወቴ እየፈራረሰ የመሰለኝ ሰዓት ነበር” ብሏል። እናቱ ግን የልጃቸው ቅስም እንዲሰበር አልፈለጉም ነበር። ዝኒች ፕሩሽኮቭ (Znicz Pruszkow) ለተባለው ክለብ እንዲጫወት አመቻቹለት።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሮበርት ሌዋንዶውስኪ ወደ ኋላ መመልከት አቆመ፤ ስኬታማ ጉዞውን ቀጠለ፤
በዝኒች ፕሩሽኮቭ የመጀመሪያ ዓመቱ 15 ጎሎችን በማስቆጠር የኮከብ ግብ አግቢነቱን ደረጃ መራ። ክለቡንም ከሦስተኛ ዲቪዚዮን ወደ ሁለተኛ ዲቪዚዮን እንዲያድግ አደረገ።
በሚቀጥለው የውድድር ዘመን ደግሞ በሁለተኛው ዲቪዚዮን 21 ጎሎችን በማስቆጠር ኮከብ ግብ አግቢ በመኾን አጠናቀቀ።
ከዚያ በኋላ በፖላንድ ከፍተኛ ሊግ ውስጥ ከሚገኙት ክለቦች መካከል የፈለገውን የመምረጥ ዕድል አገኘ። በመጨረሻም እ.አ.አ በ2008 በጋ ወቅት ሌክ ፖዝናንን (Lech Poznan) ለመቀላቀል መረጠ።
ከሌክ ፖዝናን ጋር የፖላንድ ካፕ እና ሱፐርካፕን አሸነፈ።
እ.አ.አበ2009/10 የውድድር ዘመንም ክለቡን ለሊግ ዋንጫ ክብር አብቅቷል። በግሉም የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ኾኖ አጠናቀቀ። ጊዜው ደረሰ። ሮበርት ሌዋንዶውስኪ ከፖላንድ ወጥቶ በታላላቅ ሊጎች ላይ የመጫወት አቅም እንዳለው አስመሰከረ።
በዚያን ጊዜ የጀርመኑ ክለብ ቦርሲያ ዶርትመንድ የተጫዋቾቹ ፈላጊ ኾኖ ብቅ አለ። የእንግሊዙ ክለብ ብላክበርን ሮቨርስም የተጫዋቾቹ ፈላጊ ኾኖ መጥቶ እንደነበር ይነገራል።
ነገር ግን መዳረሻው ወደ ጀርመን ኾነ። ገና 22ኛ ዓመቱ ከመሙላቱ በፊት ዶርትሙንድን የተቀላቀለው ተጫዋቹ እ.አ.አ በ2010/11 በየርገን ክሎፕ ስር የሊጉን ዋናጫ በአስደናቂ ሁኔታ ያሸነፈው ቡድን አካል ነበር።
የርገን ክሎፕ በእግር ኳስ ሕይወቱ ትልቅ አስተዋጽኦ አላቸው። በቦርሲያ ዶርትመንድ ኮከብነቱን ያሳየው ሮበርት ሌዋንዶውስኪ እ.አ.አ በ2014 የቦርሲያ ዶርትመንድ የምንጊዜም ተቀናቃኝ ክለብ ባየርን ሙኒክን ተቀላቀለ። በባየርን ሙኒክ አስደናቂ ብቃቱን ለዓለም አሳየ፤ ብስለቱ እና የእግር ኳስ ብቃቱ እያደገ ሄደ።
በተደጋጋሚ የቦንደስሊጋው ኮከብ ግብ አግቢ በመኾን አጠናቀቀ። ከባየርን ሙኒክ ጋርም የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን ጨምሮ ሌሎች ዋንጫዎችን አሳካ።
ኮከቡ በባየርን ሙኒክ ተደጋጋሚ ስኬቶችን ሲደራርብ
“ማለምን መቼም ቢኾን አታቋርጡ፤ ስትወድቁ ተስፋ አትቁረጡ። ግባችሁን ለማሳካት ጠንክራችሁ ሥሩ” ማለቱን ቦንደስሊጋው በድረ ገጹ አስፍሯል።
እ.አ.አ በ2022 ደግሞ ወደ ባርሴሎና ተዘዋወረ። ባለፉት አራት ዓመታትን ጥሩ ጊዜ አሳልፏል። በባርሴሎና ተደጋጋሚ የሀገር ውስጥ ዋንጫዎችን አሳክቷል። በባርሴሎና ቆይታው በ192 ጨዋታዎች 119 ግቦችን አስቆጥሯል።
አሁን ግን የባርሴሎና ቆይታው መጠናቀቁን አስታውቋል። እሱም እያለቀሰ፤ የባርሴሎና ደጋፊዎችም እያለቀሱ ሸኝተውታል። መዳረሻው ግን የት እንደኾነ አይታወቅም።
ኢ ኤስ ፒ ኤን ሮበርት በ21ኛው ክፍለ ዘመን ከታዩ ምርጥ አጥቂዎች መከካል አንደኛው ነው ይለዋል። ይህ ኮከብ ለታዳጊ እግር ኳስ ተጨዋቾች ታላቅ አርዓያ የሚኾን እግር ኳስ ካየቻቸው ምርጥ ተጫዋቾች መካከል አንደኛው ነው።
በታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !


