አሁን መድፉ ሠርቷል፣ የድል ተኩስም ተኩሷል።

0
25

 

ባሕር ዳር: ግንቦት 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) መድፉ ለዓመታት ኢላማውን አልመታም ነበር፤ እየሞከረ እየከሸፈበት፤ እየተኮሰ ያለ ኢላማ እየቀረበት ዓመታትን ተሻግሯል።

የመድፉ ሠራዊት ያለ ድል ታግለዋል፤ ያለ ስኬት ደክመዋል። አሁን ከዓመታት በኋላ ከድል ጋር ታርቀዋል፤ የድካማቸውን ፍሬም አግኝተዋል።

አርሰናል ለመጨረሻ ጊዜ የእንግሊዝ ፕሪምዬር ሊግ ዋንጫን ሲያሸንፍ ወጣት የነበሩት ጎልምሰዋል፤ ጎልማሶች አርጅተዋል፤ አርሰናል ለመጨረሻ ጊዜ የእንግሊዝ ፕሪምዬር ሊግ ዋንጫ ሲያሸንፍ የአርሰናል የወደፊት ኮኮብ እንደሚኾን የሚጠበቀው ማክስ ሮበርት ዶውማን አልተወለደም።

የክለቡ ኮከብ ተጫዋቾች ቡካዮ ሳካ የሁለት ዓመት ልጅ ነበር። የክለቡ አምበል ማርቲን ኦዲጋርድ ገና የአምስት ዓመት ልጅ ነበር። አርሰናል ለመጨረሻ ጊዜ የእንግሊዝ ፕሪምዬር ሊግ ዋንጫን ሲያሸንፍ አሠልጣኝ ሚኬል አርቴታ የ22 ዓመት ወጣት ተጫዋች ነበር።

22 ዓመታት በዋንጫ ረሃብ ታልፈዋል፤ ረዘም ያሉ የመውደቅ እና የመነሳት ዓመታትም ተከታትለዋል። አሁን ግን ደስታ ወደ ኤሜሬትስ ተመልሷል። ድልም መጥቷል። ለዓመታት ዋንጫ የተራበው ስታዲየም ዋንጫ አግኝቷል። ያለ ዋንጫ በታማኝነት የደገፉት የአርሰናል ደጋፊዎች በደስታ ተመልተዋል፤ ለንደን በአርሰናል ደጋፊዎች የደስታ ጭፈራ ተመልታለች።

አርሰናል ከ22 ዓመታት በኋላ የእንግሊዝ ፕሪምዬር ሊግ ዋንጫን አሸንፏል። ቢቢሲ በዘገባው ይህ ድል ለ22 ዓመታት ተጠብቋል፣ ተናፍቋልም ይላል።

አርሰናል በድረ ገጹ ሚኬል አርቴታ አርሰናልን ከተረከቡበት ጊዜ ጀምሮ በክለባችን ላይ ትልቅ ለውጥ አምጥተዋል፤ እርሷቸው ከ22 ዓመታት በኋላ የፕሪምዬር ሊግ አሸናፊ እንድንኾን መርተውናል ብሏል። በታሪኩ ለ14ኛ ጊዜ የእንግሊዝ ፕሪምዬር ሊግ ዋንጫን እንዲያሳካ ያደረጉት አሠልጣኝ ሚኬል አርቴታ በአርሰናል ታሪክ ውስጥ የማይረሳ ታሪክ ከጻፉ አሠልጣኞች መካከል አንደኛው ኾነዋል።

አርሰናልን በዋና አሠልጣኝነት ከመረከባቸው አስቀድሞ ሌላ ክለብ በዋና አሠልጣኝነት አሠልጥነው የማያውቁት ሚኬል አርቴታ ከባዱን ፈተና አልፈው ለድል በቅተዋል።

አርሰናል በድረ ገጹ ጠንካራ ቡድን የገነቡት አሠልጣኙ በድል ተራምደው ቀይ ሪባኖቻችን ከዋንጫው ጋር እንደገና እንዲጣመሩ አስችለዋል ይላል። የአውሮፓ ቀዳሚ ክለብ የመኾን ክብር ለማግኘት ከፒኤስጂ ጋር ለምንፋለምበት የቻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜም አድርሰውናል፤ በፍጻሜው ጨዋታ ካሸነፉ ይሄን ድል ያመጣ የመጀመሪያው የአርሰናል አሠልጣኝ ይኾናሉ ነው የሚለው።

ሚኬል አርቴታ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን ካሸነፉ በታሪካችን ማንም አድርጎት የማያውቀውን ያደርጋሉ ይላል።

ቢቢሲ ደግሞ አሠልጣኝ ሚኬል አርቴታ ክለቡን በአውሮፓ እግር ኳስ ውስጥ እጅግ አስደናቂ ከኾኑት አንዱ እንዲኾን አድርገውታል። በዓመታት ጥረት ጠንካራ እና አስፈሪ ክለብ ገንብተዋል ብሏል።

መድፈኞቹ የዋንጫ ፉክክሩን ቀለል የሚያደርጉባቸው ብዙ ዕድሎች እንደነበሯቸው የሚያነሳው ቢቢሲ ነገር ግን ብዙዎችን ሳይጠቀሙባቸው መቅረታቸውን አስታውሰዋል። ያባከኗቸው ዕድሎች ፉክክሩን እስከመጨረሻው ገፋው እንጂ ዋንጫ ከማሸነፍ ግን አላስቀራቸውም ይላል።

አሁን የአርሰናል የመጠበቅ ጊዜ አብቅቷል፤ ዋንጫው ከእነ ክብሩ መጥቷል፤ የድካም እና በትዕግሥት የመጠበቅ ፍሬ ተገኝተዋል። መድፉም ሠርቷል፤ ኢላማውንም መትቷል።

ኢኤስፒኤን አርሰናል በመጨረሻም ከዋንጫ ጋር ታርቋል ይላል፤ በውድድር ዘመኑ ምን አልባትም ማራኪ እግር ኳስ ተጫውቶ ላይኾን ይችላል፤ ነገር ግን ዋንጫውን ድል አድርጓል ነው ያለው። ባለፉት ተከታታይ ዓመታት ከእንግሊዝ ፕሪምዬር ሊግ ዋንጫ ደጅ እየደረሱ የተመለሱት መድፈኞቹ በመጨረሻም ተቀናቃኞቻቸውን ድል ነስተው ዋንጫውን የግላቸው አድርገዋል።

በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የአርሰናል ደጋፊዎች ደስታቸውን እያከበሩ ነው። 22 ዓመታትን ጠብቆ የመጣውን ድል እያጣጣሙ ነው።

በታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here