ባሕር ዳር: ግንቦት 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች ዋንጫ ላይ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዛሬ ሦሥተኛውን የምድብ ወሳኝ ጨዋታ ከቱኒዝያ አቻው ጋር ያደርጋል።
ብሔራዊ ቡድኑ በአፍሪካ መድረክ ከመሳተፍ ባለፈ ወደ ዓለም ዋንጫ ለማለፍ ወሳኝ የኾነውን የምድብ ጨዋታ ነው ዛሬ ምሽት 4:00 ላይ ከቱኒዚያ ጋር የሚያደርገው።
በአሠልጣኝ ቤንጃሚን ዚመር የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ቀደም ሲል ከግብጽ ጋር ያለግብ አቻ የተለያየ ሲኾን በሞሮኮ ደግሞ 2ለ1 መሸነፉ ይታወሳል።
ብሔራዊ ቡድኑ የዛሬውን ወሳኝ ጨዋታ አሸንፎ ለመውጣት ብርቱ ፉክክር እንደሚያደርግ ነው የሚጠበቀው።
ብሔራዊ ቡድኑ ለዚህ ወሳኝ ውድድር ከፍተኛ ዝግጅት ሲያደርግ የቆየ መኾኑን የኢትዮጵያ ፉት ቦል ፌዴሬሽን በማኅበራዊ ገጹ አስፍሯል።
ተጫዋቾቹም ምሽት 4፡00 ላይ ለሚካሄደው ጨዋታ ውጤታማ ለመኾን ዝግጁ መኾናቸው ተመላክቷል።
በዘንድሮው የአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች ዋንጫ ላይ 16 የአሕጉሪቱ ሀገራት የሚሳተፉ ሲኾን በውድድሩ ጥሩ ውጤት የሚያስመዘግቡ 10 ሀገራት በኳታር አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የዓለም ዋንጫ የማለፍ ዕድል የሚያገኙ ይኾናል።
በምስጋናው ብርሃኔ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !



