ባሕር ዳር፡ ግንቦት 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የደረጃ ሰንጠረዥ ፉክክር እየጠነከረ በመጣበት በዚህ ወቅት ማንቼስተር ዩናይትድ በሜዳው ኦልድ ትራፎርድ ቀን 8፡30 ላይ ኖቲንግሃም ፎረስትን የሚያስተናግድበት ተጠባቂ ጨዋታ ይካሄዳል።
ማንቼስተር ዩናይትድ ባለፈው ሳምንት ካደረገው ጨዋታ በፊት በተከታታይ ግብ የማስቆጠር መልካም ጉዞ ላይ የነበረ ሲኾን በዘንድሮው የውድድር ዘመን ቀድሞ ግብ ባስቆጠረባቸው ጨዋታዎች እስካሁን ሽንፈት አልገጠመውም።
ኖቲንግሃም ፎረስትም በተከታታይ ጨዋታዎች ሽንፈት ሳያስተናግድ በመጓዝ ላይ የሚገኝ ሲኾን ባለፈው የውድድር ዓመት በኦልድ ትራፎርድ ያስመዘገበውን ድል ለመድገም አልሞ ይጫወታል።
ክለቡ በተለይም ከሜዳው ውጭ በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ላይ ጠንካራ መኾን መቻሉ ለዛሬው ፍልሚያ መተማመኛ ኾኖታል።
የማንቼስተር ዩናይትዱ አማካይ ብሩኖ ፈርናንዴዝ በርካታ የግብ ዕድሎችን በመፍጠር በሊጉ ድንቅ የውድድር ዓመት እያሳለፈ የሚገኝ ሲኾን አዲሶቹ ፈራሚዎች ቤንጃሚን ሴስኮ፣ ማቴውስ ኩኛ እና ብራያን ምቤሞ በክለቡ የመጀመሪያ የውድድር ዘመናቸው ከፍተኛ የግብ ተሳትፎ በማድረግ የቡድኑ የፊት መስመር መሪ መኾናቸውን አስመስክረዋል።
በፎረስት በኩል ደግሞ ሞርጋን ጊብስ-ዋይት ከዩናይትድ ጋር በሚደረጉ ጨዋታዎች ላይ ግብ በማስቆጠርና በማመቻቸት ለተከላካዮች ፈተና መኾኑ የሚታወስ ሲኾን የዛሬው ጨዋታም በሁለቱ ቡድኖች መካከል ብርቱ ፉክክር እንደሚደረግበት ይጠበቃል።
በሌሎች የዛሬ የሊጉ መርሐ ግብሮች ቀን 11:00 ላይ ብሬንትፎርድ ከክሪስታል ፓላስ፣ ኤቨርተን ከሰንደርላንድ፣ ሊድስ ከብራይተን እንዲሁም ዎልቭስ ከፉልሃም ጋር የሚጫወቱ ሲኾን ምሽት 1:30 ላይ ደግሞ ኒውካስትል ዩናይትድ ዌስትሃምን ይገጥማል።
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !



