የሳዑዲ አረቢያ ትልቁ ጨዋታ !

0
25

 

ባሕር ዳር: ግንቦት 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ሳዑዲ አረቢያ ዛሬ ታላቁን የደርቢ ጨዋታ ታስተናግዳለች። የሀገሪቱ ታላላቅ ክለቦች ከዋክብት
ፍጥጫ ይጠበቃል።

ዛሬ የሚደረገው ጨዋታ የሳዑዲ ፕሮፌሽናል ሊግ የዋንጫ መዳረሻውን የሚወስን ነው። የክርስቲያኖ ሮናልዶው አልናስር እና የካሪም ቤንዜማው አል ሂላል የሚያደርጉት ጨዋታ ቀልብን ስቧል።

የደረጃ ሠንጠረዡን አንደኛ እና ሁለተኛ ኾነው የሚመሩት ሁለቱ ክለቦች ለዋንጫ ብርቱ ፉክክር ያደርጋሉ። የክርስቲያኖ ሮናልዶው አልናስር በ82 ነጥብ ሊጉን ሲመራ፣ አንድ ቀሪ ጨዋታ ያለው አልሂላል በ77 ነጥብ ይከተላል።

ክርስቲያኖ ሮናልዶ ትናንት ምሽት በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባጋራው መረጃ የእናንተ ድጋፍ በየሳምንቱ ብርታት ኾኖናል። በስታዲየም፣ በቤት እና በየትኛውም የዓለም ጥግ ኾናችሁ የምትሰጡን ኃይል ሜዳ ውስጥ አብሮን አለ። ነገን ውጤታማ እናድርገው፤ ለእኛ፣ ለእናንተ እና ለአልናስር” ብሏል።

ስፖርት ስታር በድረ ገጹ የሳውዲ ፕሮ ሊግ የዋንጫ ፉክክር እየሞቀ በሄደበት ጊዜ ዛሬ የሪያድ ደርቢ ይካሄዳል ብሏል። የዛሬው ጨዋታ ብዙ ትርጉም የሚሰጠው መኾኑን አንስቷል። ሮናልዶ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ካቀና በኋላ የሊግ ዋንጫ ማሳካት አልቻለም። የዘንድሮውን ዋንጫ ግን የሮናልዶው አልናስር የማሸነፍ ቅድመ ግምት ተሰጥቷል።

የሳውዲ ፕሮፌሽናል ሊግ በድረ ገጹ በዚህ ሳምንት የዓለም የእግር ኳስ አፍቃሪያን ዓይኖች በሙሉ በሪያድ ላይ ይኾናሉ ቢባል ማጋነን አይኾንም ብሏል።

እ.አ.አ. በ2022 የዓለማችን ተወዳጁ ተጫዋች ክርስቲያኖ ሮናልዶ ለአል ናስር መፈረሙ በሳዑዲ አረቢያ እግር ኳስ ላይ ትልቅ ለውጥ አምጥቷል ነው ያለው።

የሳዑዲ ፕሮ ሊግ በአሁኑ ወቅት በዓለም ዙሪያ በ180 ሀገራት ውስጥ በቋሚነት እንደሚታይ ጽፏል። የተመልካቾች ቁጥር በመቶ ሚሊዮኖች መኾኑን አንስቷል። ምርጡ ሊግም ኾኗል፤ ይህን ያደረገው የክርስቲያኖ ሮናልዶ ተጽዕኖ ነው ይላል።

የዛሬው የዋና ከተማዋ ደርቢም በጉጉት እንደሚጠበቅ ገልጿል። የዛሬው ጨዋታ ክርስቲያኖ ሮናልዶ በሳዑዲ ሊግ ለዓመታት ሲያልመው የነበረውን ክብር የሚያሳካበት እንደሚኾን ይጠበቃል ብሏል።

አልናስር የዛሬውን ጨዋታ የሚያሸንፍ ከኾነ ዋንጫውን ማሸነፉን ያረጋግጣል። ከተሸነፈ ግን የዋንጫ ዕድሉን አጣብቂኝ ውስጥ ያስገበዋል። ምክንያቱም አል ሂላል ቀሪውን ጨዋታ ካሸነፈ መሪነቱን ይረከባልና።

ጨዋታው ምሽት 3:00 ላይ በአልናስር ሜዳ አል አዋል ፓርክ ስታዲየም ይካሄዳል።

በታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here