ኢትዮጵያ ዛሬ የምትሳተፍበት የአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች ዋንጫ እውነታዎች !

0
21
ባሕር ዳር: ግንቦት 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች እግር ኳስ ዋንጫ በየሁለት ዓመቱ የሚካሄድ እና ዕድሜያቸው 17 ዓመት እና ከዚያ በታች የኾኑ ተጫዋቾች የሚሳተፉበት ውድድር ነው፡፡
👉 ይኼው ውድድር በፊፋ ከ17 ዓመት በታች የዓለም ወጣቶች ዋንጫ አፍሪካን የሚወክሉ ብሔራዊ ቡድኖችን ለመምረጥ ያገለግላል፡፡
👉 ፊፋ ውድድሩን ማካሄድ የጀመረው እ.አ.አ በ1985 ቢኾንም በካፍ በኩል ግን ለ10 ዓመታት ያህል በዓለም ዋንጫው የሚሳተፉ የአፍሪካ ተወካዮች የሚለዩት አንድ ሀገር ላይ በሚካሄድ ውድድር ሳይኾን በየቀጣናው በሚገኙ ሀገራት መካከል በሚደረግ የደርሶ መልስ ማጣሪያ ነበር፡፡
👉 ከ1995 ጀምሮ ግን የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ሀገራት እግር ኳስ ዋንጫ በሚል ስያሜ ውድድሩን ራሱን ችሎ በተመረጠች አስተናጋጅ ሀገር ማካሄድ ጀምሯል፡፡
👉 ከዚያ ጊዜ አንስቶ ውድድሩ 2021 ላይ በኮቪድ ወረርሽኝ ሳቢያ ሳይካሄድ ከመቅረቱ ውጭ እስካለፈው ዓመት ድረስ 15 የውድድር መድረኮችን አካሂዷል፡፡
በእነዚህ ውድድሮች ካሜሩን፣ ጋምቢያ፣ ጋና፣ ማሊ እና ናይጀሪያ እያንዳንዳቸው ሁለት ሁለት ጊዜ ሻምፒዮን ኾነዋል፡፡
ግብፅ፣ ቡርኪናፋሶ፣ ኮትዲቯር፣ ሴኔጋል እና ሞሮኮ ደግሞ አንድ አንድ ጊዜ ዋንጫውን የማንሳት ዕድል አግኝተዋል፡፡
የዘንድሮው 16ኛው የአፍሪካ ሀገራት ከ17 ዓመት በታች እግር ኳስ ዋንጫ ውድድር ከዛሬ ጀምሮ በሞሮኮ አስተናጋጅነት ይካሄዳል፡፡
በውድድሩ 16 ሀገራት በአራት ምድቦች ተደልድለው የሚፎካከሩ ሲኾን ቀይ ቀበሮዎቹ በሚል ቅፅል ስም የሚጠራው የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በመጀመሪያው ምድብ ከአስተናጋጇ ሞሮኮ፣ ግብጽ እና ቱኒዚያ ጋር ተደልድሏል፡፡
በምድብ 2 ኮትዲቯር፣ ካሜሩን፣ ኡጋንዳ እና ዲሞክራቲክ ኮንጎ፤
በምድብ 3 ማሊ፣ አንጎላ፣ ታንዛኒያ እና ሞዛምቢክ
በምድብ 4 ሴኔጋል፣ደቡብ አፍሪካ፣ አልጀሪያ እና ጋና ይገኛሉ፡፡
የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ከዚህ በፊት በዚህ ውድድር ሦሥት ጊዜ ተሳትፏል፡፡ከፍተኛ ውጤቱ በ1997ቱ መድረክ አራተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀበት ሲኾን ከዚያ ውጭ በተሳተፈባቸው ሁለት ውድድሮች የምድብ ጨዋታዎች ተሳትፎ አድርጎ ተመልሷል፡፡
ከ22 ዓመታት በኋላ ወደ ዘንድሮው ውድድር ተሳትፎ የተመለሱት ቀይ ቀበሮዎቹ ፉክክራቸውን ዛሬ 10፡00 ላይ ከግብፅ ጋር በሚያደርጉት ጨዋታ ይጀምራሉ፡፡
በዚህ ውድድር ከ1ኛ እስከ 10ኛ ደረጃን ይዘው የሚያጠናቅቁ ሀገራት ኳታር ላይ በሚካሄደው የ2026 የፊፋ ከ17 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ አፍሪካን ወክለው የሚሳተፉ ይኮናል፡፡
በኃይሌ አበራ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here