ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 29/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በጉጉት ሲጠበቅ የቆየው የ2018 ዓ.ም የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የውድድር ዘመን የማጠቃለያ መርሐ ግብር የቀን ማሻሻያ ተደርጎለት ዛሬ ሐሙስ ሚያዝያ 29/2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስታዲየም ይከናወናል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ቀደም ሲል በነበረው መርሐ ግብር ላይ ማሻሻያ ማድረጉን ተከትሎ የደረጃ እና የፍጻሜ ጨዋታዎች ዛሬውኑ ተጠናቅቀው የሊጉ ሻምፒዮና የሚለይ ይኾናል።
ዛሬ በአዲስ አበባ አበበ ቢቄላ ስታዲየም 6፡30 ላይ ጀምሮ እየተካሄደ የሚገኘው በምድብ “ሀ” ሁለተኛ ኾኖ ያጠናቀቀው የካ ክፍለ ከተማ እና ከምድብ “ለ” ሁለተኛ ኾኖ ካጠናቀቀው ደሴ ከተማ ጋር ለደረጃ እየተጫዎቱ ይገኛሉ።
ደሴ ከተማ የመጨረሻ ጨዋታውን መንጌ ቤኒሻንጉልን 2 ለ 0 አሸንፎ በከፍተኛ መነሳሳት ላይ የሚገኝ ሲኾን የዛሬውን ጨዋታ በማሸነፍ 3ኛ ደረጃን ይዞ ለማጠናቀቅ እየተጫወተ ነው።
9፡30 ላይ ደግሞ የሊጉን ዋንጫ ማን እንደሚያነሳ የሚለይበት ወሳኝ ፍልሚያ በምድብ “ሀ” አንደኛው ጋሞ ጨንቻ እና በምድብ “ለ” አንደኛው ሀላባ ከተማ መካከል ይደረጋል። የዚህ ጨዋታ አሸናፊ የ2018 ዓ.ም የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ሻምፒዮና በመኾንም ታሪክ ይጽፋል።
የፌዴሬሽኑ አሠራር እና የውድድር መርሐ ግብሮች በተደጋጋሚ ሲቀያየር በመቆየቱ ምክንያት ክለቦቹ ያለባቸውን ጨዋታ ማሸነፍ የግድ እንደኾነ በማመን ዛሬ ለሚያደርጉት ወሳኝ ፍልሚያ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጋቸው ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ድረ ገጽ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በምስጋናው ብርሃኔ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
See less



