ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በ35ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ መርሐ ግብር አርሰናል በኤምሬትስ ፉልሃምን ይጋብዛል፡፡
የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ከበላ ከ20 ዓመታት በላይ ያስቆጠረው አርሰናል የዓመታት የዋንጫ ረሃቡን ለማርካት ቀሪ አራት ጨዋታዎችን ማሸነፍ እና በጎል ከሲቲ መብለጥ ይጠበቅበታል።
የሚካኤል አርቴታው ቡድን አርሰናል ባለፈው ሳምንት ኒውካስትል ዩናይትንድን አሸንፎ ከተከታዩ ማንቸስተር ሲቲ በሦሥት ነጥብ በልጦ ሊጉን እየመራ ይገኛል።
አርሰናል ፉልሃምን ማሸነፍ ከቻለ ማንቸስተር ሲቲ ሰኞ ምሽት እስከሚጫወት የነጥብ ልዩነቱን ወደ ስድስት ከፍ ማድረግ ይችላል፡፡
ፉልሃም በበኩሉ ባሳለፍነው ሳምንት አስቶን ቪላን አሸንፎ ወደ ድል መመለሱ ይታወሳል። በአርሰናል ቤት መጫወት የቻሉ ኮከቦችን በሥብሥቡ ያካተተው ፉልሃም ጠንካራ ፉክክል እንደሚያደርግም የሚጠበቅ ነው።
አርሰናል እና ፉልሃም እርስ በእርስ ባደረጓቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች የጎላ የበላይነት አልታየም። አርሰናል ሁለቱን ሲያሸንፍ ፉልሃም ደግሞ አንዱን አሸንፏል። ቀሪ ሁለት ጨዋታዎችን ደግሞ በአቻ ውጤት ነው መለያየት የቻሉት።
በዚህ የተነሳም የሁለቱ ቡድኖች የዛሬ ግጥሚያ ብርቱ ፉክክር የሚደረግበት እንደሚኾን ይጠበቃል።
የዛሬውን ጨዋታ አስመልክቶ ንግግር ያደረጉት ሚካኤል አርቴታ “በተጫዋቾቼ ላይ የማየው ትልቅ ነገር የዋንጫ ረሃብ ነው ብለዋል። የውድድር ዓመቱን ስንጀምር ያስቀመጥነውን ግብ ለማሳካት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው አይቻለሁ ሲሉ ተደምጠዋል።
ፉልሃም ጠንካራ ተጋጣሚ ነው ያሉት ሚካኤል አርቴታ ከሻምፒዮንስ ሊጉ ጨዋታ መልስ ሙሉ ትኩረታችን ለዚህ ጨዋታ ነው ብለዋል። ደጋፊው ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ከቡድኑ ጎን እንዲኾንም ጥሪ አቅርበዋል።
የፉልሃሙ አሠልጣኝ ማርኮ ሲሊቫ በበኩላቸው አርሰናል በሊጉ ጠንካራ እና የተሟላ ሥብሥብ ያለው ቡድን ነው ብለዋል።
ቁልፍ ተጫዋቾችን በጉዳት አጥተናል ያሉት አሠልጣኝ ሲሊቫ አርሰናል ለዋንጫ የሚጫወት ቡድን ስለኾነ ያለበትን ጫና እንደ አጋጣሚ በመጠቀም ለማሸነፍ እንገባለን ብለዋል።
ጨዋታው ምሽት 1:30 በፍሌይ ኤምሬትስ ይደረጋል።
በሌላ የ35ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ቀን 11:00 የሚደረጉ ጨዋታዎችን ስንመለከት ኒውካስል ዩናይትድ ከብራይተን፤ ብሬንትፎርድ ከዌስትሃም ዩናይትድ እንዲሁም መውረዱን ያረጋገጠው ወልቭስ ከሰንደርላንድ ይጫወታሉ።
በአድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !



