ጆን ስቶንስ በውድድር ዓመቱ መጨረሻ ከማንቸስተር ሲቲ ጋር ይለያያል።

0
48

 

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በማንቸስተር ሲቲ ቤት ስኬታማ ዓመታትን ያሳለፈው እንግሊዛዊው ተጫዋች ጆን ስቶንስ በውድድር ዓመቱ መጨረሻ ከማንቸስተር ሲቲ ጋር እንደሚለያይ አስታውቋል።

ጆን ስቶንስ በውድድር ዘመኑ መጨረሻ ከማንቸስተር ሲቲ ጋር እንደሚለያይ ባሳወቀበት መልዕክቱ
በማንቸስተር ሲቲ ቤት “ሕልሞቼን ሁሉ ኖሬያቸዋለሁ ብሏል።

እ.አ.አ በ2016 በ47 ነጥብ 5 ሚሊዮን ፓውንድ ከኤቨርተን ወደ ማንቸስተር ሲቲ የተዘዋወረው ጆን ስቶንስ ላለፉት 10 ዓመታት በማንቸስተር ሲቲ ቤት ስኬታማ ጊዜን ማሳለፉን ቢቢሲ ዘግቧል።

በማንቸስተር ሲቲ ቤት ስድስት የፕሪምዬር ሊግ፣ አንድ የሻምፒዮንስ ሊግን፣ ሁለት የኤፍ ኤ ዋንጫን፣ አምስት የሊግ ካፖችን፣ ሦሥት የኮሚዩኒቲ ሺልድ ዋንጫዎችን፣ የዓለም የክለቦች ዋንጫን እና የዩኤፋ ሱፐር ካፕን አሸንፏል።

ጆን ስቶንስ ስለ ስንብቱ ባስተላለፈው መልዕክት “ማንቸስተር ሲቲ ባለፉት 10 ዓመታት ቤቴ ነበር፣ በቀሪው ሕይወቴም ቤቴ ኾኖ ይቀጥላል” ብሏል።

በብዙ መልኩ ውጣ ውረድ የበዛበት ጉዞ እንደነበር የገለጸው ተጫዋቹ የመጣው ሕጻን ልጅ ኾኖ እንደነበር እና አሁን ግን በሜዳ ላይ በጣም ስኬታማ ተጫዋች ኾኖ እየለቀቀ መኾኑን ገልጿል።

ሁሉንም ሕልሞቼን ኖሬያቸዋለሁ፣ እዚህ ስመጣ ላሳካቸው ያቀድኳቸውን ነገሮች ሁሉ አሳክቻለሁ። እዚህ በጀመርኩበት ወቅት በዚህ ደረጃ ላይ እደርሳለሁ ብዬ በፍጹም አስቤ አላውቅም ነበር ብሏል።

እያንዳንዱን ሕልሙን ከሚጠብቀው በላይ ማሳካቱንም ገልጿል።

አሠልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላም በማንቸስተር ሲቲ ያለ እርሱ ይህን ያህል ስኬታማ እኾናለሁ ብዬ አላስብም፤ ከእርሱ ጋር ይህን ያህል ረጅም ጊዜ ማሳለፍ በመቻሌ እና ሁሉንም ነገር አብሬው በማሸነፌ በጣም አመሠግነዋለሁ ብለዋል።

ክለቡ ማንቸስተር ሲቲም ጆን ስቶንስ ከስኬታማ ዓመታት በኋላ ክለቡን እንደሚለቅ አስታውቋል።

በማንቸስተር ሲቲ 293 ጨዋታዎችን ያደረገው ስቶንስ ማንቸስተር ሲቲ 19 ዋንጫዎችን እንዲያሳካ አድርጓል ብሏል።

ስቶንስ በማንቸስተር ሲቲ ቤት ያለውን ቆይታ ከማጠናቀቁ በፊት ተጨማሪ ዋንጫዎችን የማሳካት ዕድል አለው። ማንቸስተር ሲቲ ለእንግሊዝ ኤፍ ኤ ዋንጫ ለፍጻሜ ደርሷል። በእንግሊዝ ፕሪምዬር ሊግም ለዋንጫ እየተፎካከረ ነው።

ስቶንስ ሁለቱንም ዋንጫዎች ካሳካ በማንቸስተር ሲቲ ቤት ያሳካውን የዋንጫ ብዛት ወደ 21 ከፍ ያደርጋል።

ማንቸስተር ሲቲ ስቶንስ በውድድር ዓመቱ መጨረሻ እንደሚለቅ ባሳወቀበት መልዕክቱ ድንቅ ብቃት፣ ግሩም የኳስ ቅብብል ጥበብ፣ ከፍተኛ የሥራ ትጋት እና ጨዋታን የመረዳት ብቃት የታደለ ነው ብሏል።

ከተፈጥሮ ተሰጥኦው እና ከተለዋዋጭ ታክቲክ ጋር የመላመድ ብቃቱ የተነሳ ስቶንስ በሲቲ ቆይታው ሁለገብ ተጫዋቾች እንደነበር አንስቷል።

ለማንቸስተር ሲቲ እግር ኳስ ክለብ ታማኝ አገልጋይ ለነበረው ለዚህ ተጫዋች የሚገባው ክብር እና አሸኛኘት እንደሚደረግለትም ተገልጿል።

በታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here