ባሕር ዳር: ሚያዝያ 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በ34ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪምዬር ሊግ መርሐ ግብር ለዋንጫ፣ ለሻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎ እና ላለመውረድ ብርቱ ትንቅንቅ የሚደርግባቸው ጨዋታዎች የደጋፊውን ቀልብ ስበዋል።
ምሽት 1:30 አርሰናል ከኒውካስትል ዩናይትድ በኤምሬትስ ስታዲየም የሚያደርጉት ጨዋታ በበርካታ ደጋፊዎች በጉጉት ይጠበቃል።
ባለፈው ሳምንት በማንቸስተር ሲቲ ተሸንፎ ከደረጃው አናት ዝቅ ብሎ የሚገኘው የሚኬኤል አርቴታው ቡድን ኒውካስትልን አሸንፎ መሪነቱን ከሲቲ ለመረከብ ጨዋታውን ያደርጋል።
በአንጻሩ በ42 ነጥብ 14ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ኒውካስትል ዩናይትድ ደረጃውን ለማሻሻል ከጨዋታው ነጥብ ያስፈልገዋል። በዚህም ጨዋታው በጉጉት እንዲጠበቅ ኾኗል።
በመጀመሪያው ዙር ጨዋታ አርሰናል ያሸነፈ ቢኾንም የሁለቱ ቡድኖች የእርስ በእርስ ግንኙነት ብርቱ ፉክክር የሚታይበት ነው።
ባለፉት አምስት ጨዋታዎች አርሰናል ሦሥቱን ሲያሸንፉ ሁለቱን ኒውካስትል አሸንፏል።
አርሰናል በኤምሬትስ ስታዲየም ከኒውካስትል ባደረጋቸው 15 ጨዋታዎች በአንዱም አልተሸነፈም። ይህም አርሰናል በሜዳው የበላይነት እንዳለው ያሳያል። የዛሬው ጨዋታ ቅድመ ግምትም ለአርሰናል ተሰጥቶታል።
በሌላ መርሐ ግብር ፉልሃም ለሻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎ እየተጫወተ የሚገኘውን አስቶንቪላን በክራቨን ኮቴጅ ቀን 8:30 ላይ ያስተናግዳል። በተመሳሳይ ሊቨርፑል 11:00 ላይ በአንፊልድ ስታዲየም ከክሪስቲያል ፓላስ ጋር ይጫወታል።
ላለመውረድ የሚደረጉ ብርቱ ፉክክሮች የዛሬው የእንግሊዝ ፕሪምዬር ሊግ መርሐ ግብር ሌላኛው ገጽታ ነው።
በ33 ነጥቦች 17ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ዌስትሃም ዩናይትድ በለንደን ስታዲየም ኤቨርተንን ይጋብዛል። ቀድሞውኑ መውረዱን ያረጋገጠውን ወልቨርሃምተን ወንደረርስ ደግሞ በሞሊኒየክስ ስታዲየም ወራጅ ቀጣናው ውስጥ ከሚገኘው ቶትንሃም ሆትስፐርስ ጋር ይጫወታል።
ዌስትሃም ዩናይትድ ካሸነፈ ነጥቡን ከፍ አድርጎ ከወራጅ የሚርቅበት ዕድል ይኖረዋል። ቶትንሃም አሸነፎ ዌስትሃም ከተሸነፈ ደግሞ ቶትንሃም ከወራጅ ቀጣናው ወጥቶ ዌስትሃም ወራጅ ቀጣናውን የሚቀላቀል ይኾናል።
በዚህም ሁለቱ ጨዋታዎች የሞትሽረት ትግል የሚደረግባቸው እንደሚኾኑ ይጠበቃል።
ሁሉቱም ጨዋታዎች ቀን 11:00 ላይ ይደረጋሉ።
በአድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !



