ባሕር ዳር: ሚያዝያ 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ተወዳጅ የኾነው የአማራ ሊግ ውድድር በሁለት ቀጣናዎች ተከፍሎ እንደሚካሄድ የአማራ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።
የፌዴሬሽኑ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ብርሃኔ ጌትነት የአማራ ሊግ ውድድር በጸጥታ ችግሮች ምክንያት ከተቋረጠ ከሦሥት ዓመታት በኋላ በቅርብ እንደሚካሄድ ተናግረዋል።
ውድድሩ በምሥራቅ እና በምዕራብ ቀጣና ተከፍሎ ይከናወናል ነው ያሉት። የምሥራቅ ቀጣና በደሴ ከተማ አስተናጋጅነት ከሚያዝያ 25/2018 ዓ.ም እስከ ግንቦት 09/2018ዓ.ም ድረስ ይካሄዳል ብለዋል።
በደሴ ሆጤ ስታድየም በሚከናወነው የአማራ ሊግ ውድድር 10 ክለቦች እንደሚሳተፉም ገልጸዋል።
በውድድሩ አሸናፊ የኾኑ ክለቦች አማራ ክልልን ወክለው በኢትዮጵያ ክለቦች ሻምፒዮና ይሳተፋሉ ነው ያሉት።
በምዕራብ ቀጣናም ውድድሩን ለማከናወን ፌዴሬሽኑ እየሠራ ይገኛል ያሉት አቶ ብርሃኔ ክለቦችን የመመዝገብ ሥራ እየተከናወነ መኾኑንም አንስተዋል።
ተወዳዳሪዎች በስፖርታዊ ጨዋነት እንዲወዳደሩ አሳስበዋል። የደሴ እና አካባቢው ነዋሪዎች በሆጤ ስታድየም ተገኝተው ጨዋታዎችን እንዲታደሙ እና ክለቦችን እንዲያበረታቱም ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፦ ታሪኩ ዐይኔዋ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !



