ባሕር ዳር: መጋቢት 30/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአፍሪካን ጥንታዊ ማንነት እና ዕሴት ጠብቀው የቆዩ የባሕል ስፖርቶችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ እና ለማደራጀት የሚንቀሳቀሰው የአፍሪካ የባሕል ስፖርቶች እና ጨዋታዎች ኮንፌዴሬሽን (ATSGC) ዋና መሥሪያ ቤቱን ከዛምቢያ መዲና ሉሳካ ወደ ኢትዮጵያ ዋና ከተማ አዲስ አበባ ለማዛወር በፌዴሬሽኑ በኩል በተደጋጋሚ የቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት ማግኘቱን የባሕል እና ስፖርት ሚኒስቴር አስታውቋል።
ይህ ታሪካዊ ውሳኔ የተላለፈው ኢትዮጵያ በዘርፉ እያሳየች ያለችውን መሪነት እና ለባሕል ስፖርቶች የምትሰጠውን ከፍተኛ ትኩረት ተከትሎ የተሰጠ ነው። ይህም አዲስ አበባን የአፍሪካ የዲፕሎማሲ ማዕከልነቷን በተጨማሪ ስፖርታዊ ዘርፉን የምታጠናክርበት አጋጣሚ እንደሚኾን የባሕል እና ስፖርት ሚኒስቴር አስታውቋል።
የኢፌዲሪ የባሕል እና ስፖርት ሚኒስቴር ለጉዳዩ የሰጠው ከፍተኛ ድጋፍ እና ቁርጠኝነት ለዚህ ስኬት ትልቁ ምሰሶ ኾኗል ብሏል።
ዋና መሥሪያ ቤቱ ወደ አዲስ አበባ መዛወሩ ለዘርፉ እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው ተገልጿል።
መንግሥት ለባሕል ስፖርቶች የሚሰጠው ትኩረት እና ዘርፉን ከቱሪዝም ጋር በማስተሳሰር ለሀገር ገፅታ ግንባታ የሚጫወተውን ሚና በመረዳቱ ዋና መሥሪያ ቤቱ ወደ አዲስ አበባ መዛወሩ የቴክኒክ እና የአሥተዳደር ሥራዎችን ለማቀላጠፍ ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል።
ፌዴሬሽኑ በተለያዩ ክልሎች ያከናወናቸው አበረታች ሥራዎች እና ኢትዮጵያ ያሏትን በርካታ የባሕል ስፖርቶች እና ጨዋታዎችን ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ሞዴል በሚኾን መልኩ ማደራጀቱ ለውሳኔው መፋጠን ትልቅ አስተዋፅኦ አድርጓል።
ከባሕል እና ስፖርት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው ይህ ሽግግር ኢትዮጵያ በአህጉሪቱ ያላትን ስፖርታዊ ተጽዕኖ ከማሳደጉም ባለፈ የአፍሪካ የባሕል ስፖርቶች እንዲጠበቁ እና ለቀጣዩ ትውልድ እንዲተላለፉ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ኢትዮጵያ የውሳኔ ሰጪነት ማዕከል ያደርጋታል ተብሏል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



