የአፋር ባሕላዊ ስፖርት የኾነውን ‘ኮኦሶ’ የማስተዋወቅ ሥነ ሥርዓት ተካሄደ።

0
5
ባሕር ዳር: መጋቢት 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአፋር ክልል የባሕል ስፖርት የኾነው ‘ኮኦሶ’ በሐረር ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው የባሕል ስፖርቶች ውድድር እና ፌስቲቫል ላይ ለተሳታፊዎች የማስተዋወቅ ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል።
በኢትዮጵያ የባሕል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ሕግ እና ደንብ ተዘጋጅቶላቸው 11 የባሕል ስፖርቶች ውድድር እየተደረገባቸው ይገኛል።
በእርግጥ በኢትዮጵያ ከ290 በላይ የባሕል ስፖርቶች እንዳሉ ይታመናል።
የኢትዮጵያ የባሕል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ከዚህ በፊት ተጠንተው ወደ ውድድር ከመጡት 11ዱ በተጨማሪ ሌሎች የባሕል ስፖርቶችን በማጥናት ወደ ውድድር ለማምጣት ጥረት እያደረገ ይገኛል።
ከእነዚህ መካከል አንዱ የአፋር ባሕላዊ ስፖርት የኾነው ‘ኮኦሶ’ ይገኝበታል።
ከዚህ በፊት በሆሳዕና ከተማ በተካሄደው የባሕል ስፖርቶች ውድድር የተዋወቀው ይሄው ስፖርት በሐረር አዘጋጅነት እየተካሄደ በሚገኘው የውድድር መድረክ የአፋር ወጣቶች በሁለት ቡድን ተከፍለው በመጫወት ስፖርቱን ለታዳሚዎች አስተዋውቀዋል።
‘ኮኦሶ’ በአፋር ከሚገኙ በርካታ ባሕላዊ ጨዋታዎች መካከል አንዱ ሲኾን የወንዶች ኳስ ሽሚያ እና ቅብብል ጨዋታ በመባል ይታወቃል።
‘ኮኦሶ’ በአፋርኛ ኳስ እንደማለት ሲኾን ጨዋታው አካላዊ ጥንካሬ በቴክኒክ እና ታክቲክ በልጦ መገኘትን የሚጠይቅ የስፖርት ዓይነት ነው።
በጨዋታው የተሳታፊ ቁጥር ገደብ ባይኖረውም በቁጥር ግን እኩል ለማድረግ ይሞከራል። ጨዋታው አነስተኛ ኳስን ይጠቀማል።
ኳሱም ከለሰለሰ የፍየል ቆዳ በክብ ቅርጽ ይዘጋጃል። በውድድሩ ለመካፈል የዕድሜ ገደብ ባይኖርም ጨዋታው የልጆች እና የአዋቂዎች በመባል ይከፋፈላል፡፡
የ’ኮኦሶ’ ጨዋታ ተወዳዳሪ ቡድኖች ፊት ለፊት ከቆሙ በኋላ ኳሷን አንድ ሰው አንጥሮ ጨዋታውን ይጀምራል፡፡
ኳሷን ያነጠረው ሰው ጨዋታው ከተጀመረ በኋላ ኳሷን ይዞ ሲሮጥ እሱን ለመጣል በሚደረግ ትግል ጨዋታው ይቀጥላል፡፡
ከቡድኑ አባላት መካከል ኳስ በመቀባበል ማለትም በተቃራኒው ቡድን ኳስን ሳያስነጥቅ ብዙ መቆየት የቻለ ቡድን አሸናፊ ይኾናል፡፡
የባሕል እና ስፖርት ሚኒስቴር ከባሕል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ጋር በመኾን ይህን የአፋሮች ባሕላዊ ጨዋታ ወደ ውድድር ለማምጣት ሕግ እና ደንብ እያዘጋጀ ይገኛል።
ወደ ውድድር ለማምጣትም ሥራዎች ተጀምረዋል። በቀጣይ ዓመት 12ኛ የባሕል ስፖርት አድርጎ የማቅረብ ዕቅድ መኖሩም ተመላክቷል።
ዘጋቢ፦ ኃይሉ አዳነ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here