ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄደውን የአፍሪካ የባሕል ስፖርት ጨዋታዎች ለማዘጋጀት ተመረጠች።

0
6
ባሕር ዳር: መጋቢት 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ባሕል ስፖርቶች ፌዴሬሽን በቅርቡ የአፍሪካ ባሕል ስፖርቶች እና ጨዋታዎች ኮንፌዴሬሽን የአባልነት ጥያቄ ተቀባይነት ማግኘቱ ይታወሳል።
ትናንት መጋቢት በ20/2018 ዓ.ም ደግሞ የኢትዮጵያ ባሕል ስፖርቶች ፌዴሬሽን እና የአፍሪካ ባሕል ስፖርቶች እና ጨዋታዎች ኮንፌዴሬሽን ጋር በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት ተፈራርመዋል።
በስምምነቱ ኢትዮጵያ በ2026 የሚካሄደውን የመጀመሪያውን የአፍሪካ ባሕል ስፖርቶች እና ጨዋታዎች ፌስቲቫል በአዲስ አበባ ታዘጋጃለች።
ፌስቲቫሉ አፍሪካውያን ተሳታፊዎች ባሕላቸውን እና የባሕል ስፖርቶቻቸውን የሚያስተዋውቁበትን ዕድል ይፈጥርላቸዋል።
በመግባቢያ ሥነ ሥርዓቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የባሕል እና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ መኪዩ መሐመድ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄደው የባሕል ስፖርቶች እና ጨዋታዎች ፌስቲቫል በኢትዮጵያ መካሄዱ ተደጋጋሚ ዓለም አቀፍ የስፖርት ሁነቶችን ላስተናገደችው ኢትዮጵያ ተጨማሪ መልካም አጋጣሚ ነው ብለዋል።
ውድድሩ አህጉራዊ ትስስርን የሚያሳድግ በመኾኑ በሚገባ እንጠቀምበታለን ነው ያሉት።
የአፍሪካ ባሕል ስፖርቶች እና ጨዋታዎች ኮንፌዴሬሽን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት እና የኢትዮጵያ ባሕል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ሕይወት መሐመድ የተሻለ የስፖርት መሠረተ ልማት ባለባት አዲስ አበባ ፌስቲቫሉን ለማካሄድ መወሰኑ ለኢትዮጵያ የባሕል ስፖርቶች አዲስ ምዕራፍ መኾኑን አመላክተዋል።
ሀገር በቀል ጨዋታዎቻችንን ለዓለም ለማሳየት እና በስፋት ለማስተዋወቅ መልካም ዕድል መኾኑንም አመላክተዋል።
የአፍሪካ ባሕል ስፖርቶች እና ጨዋታዎች ኮንፌዴሬሽን ሊቀመንበር ኪይካማቱዋ ፒተር (ዶ.ር) ኢትዮጵያ የበርካታ ባሕሎች መገኛ መኾኗ የአስተናጋጅነት ዕድልን አስገኝቶላታል ብለዋል።
ፌስቲቫሉንም የአፍሪካውያንን አንድነት እና ኅብረት ለማጠናከር እንጠቀምበታለን ነው ያሉት።
በመግባቢያ ሰነዱ መሠረት ሁለቱ ተቋማት በቴክኒክ ድጋፍ፣ በሚዲያ አጠቃቀም፣ በባሕላዊ ጨዋታዎች ሕግጋት ዝግጅት እና በሥልጠና ዙሪያ በቅርበት ይሠራሉ ተብሏል።
ዘጋቢ፦ኃይሉ አዳነ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here