ኢትዮጵያ ሚያዝያ 2018ዓ.ም በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድርን ታስተናግዳለች።

0
55

 

አዲስ አበባ: መጋቢት 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድርን ሚያዝያ 2018ዓ.ም እንደምታስተናግድ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።

ኢትዮጵያ የምታስተናግደውን የአንድ ቀን ኮንቲኔንታል ቱር በተመለከተ እና በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ የሰጡት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አትሌት ስለሽ ስህን ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን የማስተናገድ አቅምን እየፈጠረች ነው ብለዋል።

አዲስ አበባ ግራንድ ፕሪ በሚል ስያሜ ሚያዝያ 10/2018 ዓ.ም ለሚካሄደው ኮንቲኔንታል ቱር አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መኾኑንም ገልጸዋል።

የነሐስ ደረጃ የተሰጠው እና በኢትዮጵያ አዲስ አበባ የሚካሄደው የአንድ ቀን ኮንቲኔንታል ቱር ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል። ውድድሩን በስኬት ለማዘጋጀትም ከወርልድ አትሌቲክስ ጋር በቅርበት እየተሠራ መኾኑንም አመላክተዋል።

የአደይ አበባ ስታዲየም ዘመናዊ ስታዲየም መኾኑን የተናገሩት አትሌት ስለሽ ስህን ከሀገር አልፎ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን የማስተናገድ አቅም ያለው መኾኑን ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ስታዲየም ትራክ በቅርቡ እንደሚጠናቀቅም አስታውቀዋል። በቀጣይ ሌሎች ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ለማስተናገድ ዝግጅት እየተደረገ መኾኑንም ተናግረዋል።

የ2029 እና 2031 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናን ለማስተናገድ አስፈላጊው ዶክሜንት መዘጋጀቱን ጠቁመዋል። በተጨማሪም በ2028 የሚካሄደውውን አልትሜት ሻምፒዮን ሽፕ ለማዘጋጀትም ፌዴሬሽኑ በዝግጅት ላይ ነው ብለዋል።

በቅርቡ በኢትዮጵያ ጉብኝት ያደረጉት የዓለም አትሌቲክስ የውድድር ዋና ዳይሬክተር ፒርስ ኦክላጋን ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ውደድሮችን ለማዘጋጀት በቂ አቅም እንዳላት ማረጋገጣቸውንም ፕሬዝዳንቱ አስታውሷል።

ዘጋቢ: ባዘዘው መኮነን

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here