ሁመራ: የካቲት 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ከነጻነት በኋላ ለሦስተኛ ጊዜ የተካሄደው የዞኑ መላው ስፖርታዊ ጨዋታ ፍጻሜውን አግኝቷል።
ጨዋታው በዳንሻ ከተማ አሥተዳዳር አስተናጋጅነት የተካሄደ ሲኾን በስድስት የስፖርት ዓይነቶች አስር ክለቦች ተሳትፈዋል።
የዳንሻ ከተማ እና የሰቲት ሁመራ ከተማ የእግር ኳስ ክለቦች በተገናኙበት የፍጻሜ ጨዋታ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የዞኑ ምክትል አሥተዳዳሪ እና የሰላምና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ስፖርት ለፍቅር፣ ለሰላም እና ለአንድነት ግንባታ አስፈላጊ መኾኑን አንስተዋል።
ኮሎኔል ደመቀ አክለውም የጨዋታው አስተናጋጅ የዳንሻ ከተማ ሕዝብ፣ የዞኑ ሕዝብ ለነጻነቱ ባደረገው ተጋድሎ ትልቅ ድርሻ እንዳለው ጠቅሰው ይሄንን ውድድር በነጻነት ለማከናወን መስዋእት ለከፈሉ ወገኖች ምስጋና አቅርበዋል።
ከውድድሩ ብዙ ነገር ተምረናል ያሉት ደግሞ የዳንሻ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አብዱልዋሀብ ማሙ ናቸው። ስፖርት የሕዝብን አንድነት የሚያጠናክር፣ ማኅበራዊ ትስስርን እንደሚያጎለብት፣ የጋራ ችግሮችን መፍታት እንደሚያስችል እና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታውም ከፍ ያለ መኾኑን ከንቲባው ገልጸዋል።
የዘንድሮውን ውድድር በማሸነፍ ዋንጫ በማንሳታቸው ደስተኛ መኾኗን የዳንሻ ከተማ የሴቶች መረብ ኳስ ክለብ ተጨዋቿ ፍሬ ስማቸው ለአሚኮ ተናግራለች። የውድድር ስሜቱ ከፍተኛ መኾኑን ያነሳቸው ተጨዋቿ ከውድድር ባሻገር የእርስ በእርስ ትብብር እና አንድነት ጎልቶ የታየበት እንደነበርም ጠቅሳለች።
የማይካድራ አትሌትክስ ክለብ የአጭር ርቀት ሯጩ ተመስገን ጌትነት በ100 ሜትር የብር እና በ200 ደግሞ የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ በመኾኑ የተሰማውን ደስታ ገልጿል። ከዚህ በፊት በእግር ኳስ ተሳታፊ እንደነበረ ያስታወሰው ሯጩ ለመጀመሪያ ጊዜ በተወዳደረበት የሩጫ ውድድር ማሸነፍ በመቻሉ ያለውን ተስፋ ተናግሯል።
ሀገር የመወከል ታላቅ ሕልም እንዳለው ጠቅሶ ለዚህም ጠንክሮ እንደሚሠራ ነው የተናገረው።
በሦስተኛው መላው የዞኑ ስፖርታዊ ውድድር ሰቲት ሁመራ ከተማ በአምስት ወርቅ እና በሁለት ብር፤ ዳንሻ ከተማ አሥተዳደር በሦስት ወርቅ፣ በአራት ብር እና በሁለት ነሐስ፤ ወልቃይት ወረዳ በሦስት ወርቅ እና በአንድ ብር በቅደም ተከተል ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል።
ወልቃይት ወረዳ አራተኛውን መላ የዞኑ ጨዋታ ለማዘጋጀት ተመርጧል።
ዘጋቢ:- አምሳሉ አሞኘ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን



