በወርቆች የደመቀችው ታዳጊዋ ዋናተኛ!

0
44
አዲስ አበባ: የካቲት 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአዳማ ከተማ በተካሄደው የታዳጊዎች ምዘና ውድድር በውኃ ዋና ስፖርቶች ውድድር የታየችው በፍቅር እጅግሰው የውድድሩ ክስተት ኾናለች።
የመዋኛ ገንዳውን በተለያዩ ውድድሮች የተመላለሰችው ኮምቦልቻ ያፈራት ታዳጊ 12 ወርቆችን ሰብስባለች። በፍቅር ውኃ ዋና ስፖርትን ገና በልጅነት እድሜዋ ማዘውተር ስትጀምር ኮምቦልቻ አካባቢ የወጡ ስፖርተኞችን በማየት ነው።
በአሠልጣኝ ኢስማኤል መሐመድ ድጋፍ ልምምዴን እሠራለሁ፤ ብዙ ክፍተቶችን እየሞላ ብቁ እንድኾን አድርጎኛል የምትለው በፍቅር በታዳጊዎች የምዘና ውድድር ላይ አማራ ክልልን በውኃ ዋና ስፖርት በማስጠራቷ ደስተኛ መኾኗን ገልጻልናለች።
እንደዚህ አይነት ውድድሮች ለታዳጊዎች የተሻለ እድል የሚሰጡ እና አቅማቸወን ለማየትም የሚረዳ መኾኑን ተናግራለች።
በአዳማው ውድድር ከፍ ብላ የታየችው ታዳጊ ህልሟ ከፍ ያለ ነው። በፍቅር በዚሁ ስፖርት “ሀግሬን በዓለም አቀፍ መድረክ የማስጠራት ሕልም አለኝ፤ ለዚህ ደግሞ ጠንክሬ እሠራለሁ” ብላለች።
በውድድሩ በአሠልጣኝነት የውኃ ዋና ልዑኩን ከመሩት አሠልጣኞች አንዱ የኾነው ኢስማኤል መሐመድ በፍቅር በዚህ ውድድር መድረክ እንድትደምቅ ቤተሰቦቿ ድጋፋቸው ከፍ ያለ ገልጸዋል። በቀጣይም በውኃ ዋና ስፖርት ከፍ ያለ ቦታ እንደምትደርስ ተናግረዋል።
በዚህ ውድድር ያስመዘገበችው ውጤትም ለሌሎች ታዳጊዎች መነቃቃትን የሚፈጥር ነው ብለዋል።
በፍቅርም አሠልጣኟን እና ቤተሰቧን እንዲሁም ኮምቦልቻ ጨርቃ ጨርቅን አመስግናለች። በቀጣይ በትልቅ ውድድር ሌላ ክስተት ኾና ብቅ እንደምትልም የብዙዎች እምነት ነው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here