በናይጄሪያ አቡኩታ ከተማ በተካሄደው የአፍሪካ ከ20 እና 18 ዓመት በታች ሻምፒዮና ላይ ለተሳተፋት እና አበረታች ውጤት ላስመዘገበው የአትሌቲክስ ልዑክ ቡድን የእውቅናና የሽልማት መርሐ ግብር ተካሂዷል፡፡
በውድድሩ ላይ አበረታች ውጤት ላስመዘገበው ልዑክ ቡድን የማበረታቻ ሽልማት ተበርክቷል ።
በመርሐ ግብሩ ላይ የቡዱኑ መሪ ኢንስትራክተር አድማሱ ሳጂ ስለነበራቸው ቆይታ አብራርተዋል። ኢንስትራክተሩ በብዙ ችግር ውስጥ ተፈትኖ ጥሩ ውጤት ላመጡት የቡድኑ አባላትን አመስግነዋል ።
በተጨማሪም የቡድኑ ቴክኒክ ቡድን መሪ ጊዜ አድነው፣ አሠልጣኝ መሰረት መንግሥቱ፣ በሻምፒዮናው የወርቅ እና ብር ሜዳልያ አሸናፊ እና በ1500 ወንዶች አትሌት ሳሙኤል ስለነበራቸው አጠቃላይ የውድድር ኹኔታ አንስቷል።
የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ኮማንደር አትሌት ስለሺ ስህን ልዑክ ቡድኑ ያስመዘገበው ውጤት ጥሩ መኾኑን አንስተዋል ።
በዕድሜ ተገቢነት ምርመራ ላይ የወሰደው ቆራጥ እርምጃ ለብዙ የአፍሪካ ሀገሮች በተሞክሮ ሊወሰድ የሚችል እንደኾነ ተናግሯል ።
ፕሬዝዳንቱ በተተኪ አትሌቶች ላይ ፌዴሬሽኑ በትኩረት እንደሚሠራ በማንሳት፣ ለዓመታት ችግር ኾኖ የቆየው የትራክ እና የማዘውተሪያ ስፍራ እጥረት በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተሠራ ነውም ብለዋል።
ኢትዮጵያ በውድድሩ ላይ በ28 አትሌቶች ተሳትፋ ሁለት ወርቅ፣ ሦስት ብር እና አምስት ነሃስ በአጠቃላይ 10 ሜዳልያዎችን አስመዝግባለች።