“የምወደውን እና የምጓጓለትን አረንጓዴ ፣ቢጫ እና ቀዩን ሰንደቅ አላማ ወክዬ የምጫወትበት ጊዜ እንዳበቃ ይሰማኛል”ጥበበኛው እግር ኳሰኛ”ሽመልስ በቀለ

0
281

ባሕርዳር: ታኅሳሥ 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ሽመልስ በቀለ ለ15 ዓመታት ካገለገለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ራሱን ማግለሉን ይፋ አድርጓል።

“የምወደውን እና የምጓጓለትን አረንጓዴ ፣ ቢጫ እና ቀዩን ሰንደቅ አላማ ወክዬ የምጫወትበት ጊዜ እንዳበቃ ይሰማኛል። ከትልቅ አክብሮት ጋር የብሔራዊ ቡድን ጉዞዬን እዚህ ጋር ለማብቃት ወስኛለሁ፤ እዚህ ውሳኔ ላይ ስደርስ እና ለስፖርት አፍቃሪው ሳጋራ ከትልቅ ከበሬታ ጋር ነው።

የሀገራችንን ባንዲራ ከፍ ለማድረግ በተጫወትኩበት አጋጣሚዎች ሁሉ ከቡድን አጋሮቼ ጋር ያሳለፍናቸውን አጋጣሚዎች ሁሌም የማልረሳቸው እና በታሪክነት ይህ አርማ ፣ ማልያ እና ስፖርት አፍቃሪው እንዲሁም መላው ኢትዮጵያዊ ለሀገሬ በምጫወትበት እያንዳንዱ አጋጣሚ ያሳያችሁኝ ፍቅር ሁሌም ደስተኛ አድርጎኛል።

ሀገሬን እንድወከል የመጀመሪያውን ጥሪ ካቀረቡልኝ አሰልጣኝ አብርሀም ተክለማርያም ጀምሮ እስከ መጨረሻው አሰልጣኝ ገብረ መድኅን ሀይሌ እና በብሔራዊ ቡድን ያሠለጠናችሁኝ መላው አሠልጣኞች እና የአሠልጣኝ ቡድን አባላት ያለኝን አክብሮት እና ምስጋና ለመግለፅ እወዳለሁ።

በብሔራዊ ቡድን ቆይታዬ ከሰላሳ አንድ ዓመታት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ ሲያልፍ የቡድን አባል መኾኔ አሁንም ሳስበው ልዩ ስሜትን ይፈጥርልኛል።

በቆይታዬ ብሔራዊ ቡድናችንን ህዝቡ እንደሚጠብቀው በዓለም ዋንጫ መሳተፍ እና በአፍሪካ ዋንጫ ውድድር የተሻለ ውጤት አለማስመዝገባችን የሚያስከፋኝ እና የሚቆጨኝ ነው።

“በቀጣይ የሚመጣው ትውልድ እና የቡድን አጋሮቼ ይህን እንደሚያሳዩ ትልቅ እምነት ያለኝ ሲሆን እኔም ይህ እንዲሳካ ከተጫዋችነት ውጪ ከጎን መኾን እንደምችል አረጋግጣለሁ።

በዚህ ጉዞዬ ውስጥ የነበሩ የ ኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንቶች ፣ ሥራ አሥፈፃሚ እና መላው ሠራተኞች ታሳዩኝ ለነበረው ፍቅር አክብሮቴን እገልፃለሁ። በቀጣይም ከሀገሬ እና ብሔራዊ ቡድኑ ጎን በመኾን በስሜት እና በኩራት ዋልያዎቹን የማበረታታ መኾኔን ለመግለፅ እወዳለሁ። ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻዋ ቀን በእኔ እምነቱ ኖሯችሁ ከጎኔ ለነበራችሁ ሁሉ ልባዊ ምስጋናዬ ይድረሳችሁ።” ሲል በይፋ ስንብቱን አሳውቋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here