“የባሕር ዳር ስታዲየም በቀጣይ መስከረም የሚጀመረውን የ2027 የአፍሪካ ዋንጫ ምድብ ማጣሪያ እንዲያስተናግድ እየሠራን ነው” የባሕል እና ስፖርት ሚኒስቴር

0
59
ባሕል እና ስፖርት ሚኒስቴር በ2018 በጀት ዓመት በስፖርቱ ዘርፍ ያከናወናቸው ተግባራትን እየገመገመ ነው።
ከሐምሌ 29/2018 ዓ.ም እስከ ነሐሴ 01/2018 ዓ.ም በሚቆየው መድረክ ጅማ ዩኒቨርሲቲ ስፖርት፣ ባሕል እና ኪነጥበብን በሚመለከት ባጠናው ጥናት ላይ ውይይት የሚደረግ ሲኾን የቀጣይ ሦሥት ዓመት አቅጣጫዎችም ይቀመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የባሕል እና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ በሁሉም ሴክተሮች በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል ብለዋል።
በተለይ በዓመቱ ለ28 ዓመታት ሥራ ላይ የነበረው የስፖርት ፖሊሲ የተሻሻለበት ዓመት መኾኑን ሚኒስትሯ አንስተዋል። አዲሱ የስፖርት ፖሊስ የስፖርት ልማት ተወዳዳሪነትን ይበልጥ ከፍ የሚያደርግ መኾኑንም ተናግረዋል።
ከታዳጊዎች ልማት ጋር በተያያዘ በርካታ ሥራዎች መከናዎናቸውን የተናገሩት ሚኒስትሯ የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎችን ተደራሽ በማድረግ በኩልም መንግሥት ትኩረት ሰጥቷል ብለዋል። አሁን ላይ በመላ ሀገሪቱ ከ45 ሺህ በላይ የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች መኖራቸውንም ጠቁመዋል።
ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን ማስተናገድ የሚችሉ ስታዲየሞችን ለማድረስ በትኩረት እየተሠራ እንደኾነ እና የባሕር ዳር ስታዲየም በቀጣይ መስከረም የሚጀመረውን የ2027 የአፍሪካ ዋንጫ ምድብ ማጣሪያ እንዲያስተናግድ ለማድረግ ሥራዎች በፍጥነት እየተሠሩ መኾኑንም አመላክተዋል።
የባሕል እና ስፖርት ሚኒስትሯ ሸዊት ሻንካ፣ አደይ አበባ ስታዲየም ጥራቱን በጠበቀ መልኩ ግምባታው መቀጠሉን ገልጸው በቀጣይም ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን ማስተናገድ የሚችሉ እና የካፍን መመዘኛ የሚያሟሉ ስታዲየሞችን ለማድረስ ትኩረት ይደረጋል ብለዋል።
በ2018 በጀት ዓመት በርካታ አህጉር እና ዓለም አቀፍ ስፖርታዊ ውድድሮች በሀገራችን መካሄዳቸውን እና በቀጣይም ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን እና ጉባኤዎችን ለማካሄድ ቀጠሮ መያዟን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ በ2027 የዓለም አቀፉ ስፖርት ጋዜጠኞች ማኅበር ጉባኤን እና የፀረ ዶፒንግ ኮንፈረንስን እንደምታስተናግድም አስታውሰዋል።
✍️ዘጋቢ፦ ባዘዘው መኮንን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here