በተለያዩ ዘመናት ግርምትን አጭረው ካለፉ የዓለም ዋንጫ ክስተቶች ውስጥ !

0
17

 

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የዓለም ዋንጫ ታሪክ በአስደናቂ ግቦች እና በደስታ እምባዎች ብቻ የተሞላ አይደለም። ከጀርባው ብዙ የማይነገሩ፣ ግርምትን እና ሳቅን የሚያጭሩ ለየት ያሉ ትዕይንቶችም ይከሰቱበታል።

እ.አ.አ 1982 በነበረው የስፔን የዓለም ዋንጫ ጨዋታ ኩዌት እና ፈረንሳይ ሲጫወቱ አንድ አስገራሚ ነገር ተፈጠረ። ፈረንሳይ 4ኛ ግብ ስታስቆጥር የኩዌት ተከላካዮች “ከሜዳው ውጭ የዳኛ ፊሽካ ድምጽ ሰምተን ነው የቆምነው” በማለት መቃወም ጀመሩ። በዚህ ጊዜ የኩዌት እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት የነበሩት ሼክ ፋሃድ አል-አህመድ አል-ሳባህ ከተቀመጡበት ወንበር ወርደው በቀጥታ ወደ ሜዳ ገቡ።

ዳኛውን በማስፈራራት እና ተጫዋቾቻቸውን ከሜዳ እንደሚያስወጡ በመዛት ዳኛው ያስቆጠሩትን ግብ እንዲሰርዙ አደረጉ። ይህም በዓለም ዋንጫ ታሪክ አንድ የውጭ አካል ሜዳ ገብቶ የዳኛን ውሳኔ ያስቀየረበት ብቸኛው አስገራሚ ትዕይንት ነው።

በ1958ቱ የሲዊድን የዓለም ዋንጫ ደግሞ ብራዚል ከሲዊድን ጋር ለመጨረሻ ጨዋታ ደረሰች። ነገር ግን ሁለቱም ቡድኖች ቢጫ ማሊያ በመልበሳቸው ምክንያት ዕጣ ተጣጥለው ብራዚል ማሊያዋን እንድትቀይር ተገደደች። ብራዚል በወቅቱ ተቀያሪ ሰማያዊ ማሊያ ይዛ አልመጣችም ነበር።

የቡድኑ አባላት ከጨዋታው ጥቂት ቀናት በፊት በስቶክሆልም ከተማ ሱቆች እየዞሩ ሰማያዊ ማሊያዎችን በገንዘብ ገዙ። ከዚያም የብራዚልን አርማ እና የተጫዋቾችን ቁጥር በምሽት በእጅ ሰፍተው አዘጋጁት። የሚገርመው፣ በዚያ በችኮላ በተገዛ “የሱቅ ማሊያ” ብራዚል ሲዊድንን 5 ለ 2 በማሸነፍ ለመጀመሪያ ጊዜ የዓለም ዋንጫን አነሳች።

በእግር ኳስ ሕግ አንድ ተጫዋች ሁለት ቢጫ ካርድ ካገኘ በቀይ ካርድ ከሜዳ መውጣት እንዳለበት ይታወቃል። ነገር ግን በ2006ቱ የጀርመን የዓለም ዋንጫ ደግሞ ክሮሺያ ከአውስትራሊያ በምታደርገው ጨዋታ ይሄ ሕግ ተጣሰ።

እንግሊዛዊው ዳኛ ግርሃም ፖል፣ ክሮሺያዊው ተከላካይ ጆሲፕ ሲሙኒች ላይ በ61ኛው እና በ90ኛው ደቂቃ ላይ ቢጫ ካርድ ቢያሳዩም በቀይ ካርድ ከሜዳ ማሰናበት ረሱት። ጉዳዩ የታወቀው ግን የጨዋታው መደበኛ ሰዓት አልቆ በተጨማሪ በ93ኛው ደቂቃ ላይ ሲሙኒች ዳኛውን በመቃወሙ ለሦሥተኛ ጊዜ ቢጫ ካርድ ተሰጥቶት በመጨረሻም ቀይ ካርድ አይቶ በመውጣቱ ነበር። ይህ ትዕይንት ግን ዳኛውን ከጨዋታ ያሰናበተ ስህተት ነበር።

የአሚኮ ቤተሰቦች እስኪ እናንተም የምታውቁትን ለየት ያለ አስገራሚ የዓለም ዋንጫ ታሪክ አጋሩን?

#አሚኮ_ዜና #ስፖርት

ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here