ባሕር ዳር: ግንቦት 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የ2025/26 የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ የውድድር ዘመን ዛሬ ምሽት በሚደረጉ የመጨረሻ ዙር ጨዋታዎች ፍጻሜውን ያገኛል። አርሰናል ከ22 ዓመታት ቆይታ በኋላ የሊጉን ዋንጫ ማንሳቱን ቀድሞ ቢያረጋግጥም፤ የዛሬዎቹ ጨዋታዎች ወደ አውሮፓ መድረክ የሚያልፉትን እና ሦሥተኛውን ወራጅ ክለብ የሚለዩ በመኾናቸው ከፍተኛ ትኩረትን ስበዋል።
በሰንጠረዡ አናት አርሰናል፣ ማንቸስተር ሲቲ እና ማንቸስተር ዩናይትድ ከአንድ እስከ ሦሥት ያለውን ደረጃ በመያዝ የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎአቸውን አረጋግጠዋል። በሌላ በኩል አስቶን ቪላ የዩሮፓ ሊግ ዋንጫን ማሸነፉን ተከትሎ፣ እንግሊዝ እስከ 6 ክለቦችን በሻምፒዮንስ ሊግ የምታሳተፍበት ታሪካዊ ዕድል ተፈጥሯል።
ይህንን ተከትሎ በዛሬው ጨዋታ ሊቨርፑል ካሸነፈ እና አስቶን ቪላ ከተሸነፈ ሊቨርፑል 4ኛ ደረጃን የሚይዝ ሲኾን፤ የ6ኛ ደረጃ ባለቤት የሚኾኑት ቦርንማውዝ ወይም ብራይተን 6ኛው የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊ የመኾን ዕድል ይኖራቸዋል። ቦርንማውዝ 6ኛነቱን ለማረጋገጥ 1 ነጥብ ብቻ የሚያስፈልገው ሲኾን፣ ብራይተን ደግሞ ዩናይትድን አሸንፎ የቦርንማውዝን መሸነፍ ይጠብቃል። ቼልሲ በበኩሉ ሰንደርላንድን ካሸነፈ የኮንፈረንስ ሊግ ተሳትፎውን ያረጋግጣል።
በሰንጠረዡ ግርጌ ዎልቨርሃምፕተን እና በርንሌይ መውረዳቸውን ያረጋገጡ ሲኾን፣ ሦሥተኛው ወራጅ ክለብ ላለመኾን በለንደን ተቀናቃኞቹ ቶተንሃም እና ዌስትሃም መካከል ከባድ ፉክክር ይጠበቃል።
በ17ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቶተንሃም ዛሬ ከኤቨርተን ጋር አቻ ከተለያየ በሊጉ መቆየቱን ያረጋግጣል። በአንጻሩ በ18ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ዌስትሃም በሊጉ ለመሰንበት ዛሬ ሊድስን የግድ ማሸነፍ እና ቶተንሃም መሸነፍ ይኖርበታል።
የሊጉ የመጨረሻ ሳምንት ጨዋታዎች በሙሉ ዛሬ ምሽት በተመሳሳይ 12፡00 የሚካሄዱ ይኾናል።
ዘጋቢ፦ ሀብታሙ ዳኛቸው
#አሚኮ_ዜና #ስፖርት #የእንግሊዝ_ፕሪምየርሊግ #ዓለም
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !


