“ሰው የምንስበውም፤ የምንገፋውም እኛው ነን…” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ

116

ባሕር ዳር፡ መስከረም 27/2013ዓ.ም (አብመድ) ባሕር ዳር ከተማን የበለጠ የኢንዱስትሪና የቱሪዝም ከተማ ማድረግ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶክተር) አስታወቁ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የባሕር ዳር ኢንዱስትሪ ፓርክን በመረቁበት ሥነ ሥርዓት ላይ ባሕር ዳር በተፈጥሮ ውብ መሆኗ ለበለጠ ኢንቨስትመንት እና ቱሪዝም ምቹ እንደሚያደርጋት ገልጸዋል፡፡ በተፈጥሮ ያልታደሉ ቦታዎችን ውብ አድርገው የሚስደምሙ በርካታ ሀገራት መኖራቸው በመጥቀስም ባሕር ዳርን ትንሽ በመሥራት ብዙዎችን የምትስብ፣ ሕይወትን የምታሻሽል፤ የሥራ ዕድል የምትፈጥር ማድረግ እንደሚቻል አስገንዝበዋል፡፡

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ የኢፌዴሪ መንግሥት በጎርጎራ ቀጣይ የሚጀመረው የቱሪዝም ልማት ሥራ ጎብኝዎች ወደ ባሕር ዳር አቅንተው በውበቷ እንዲደነቁ፣ የሕዝቡን ሰላም እና ሥራ ወደዳድነት ዓይተው ሀብት እና ዕውቀታቸውን ፈሰስ እንዲያደርጉ የሚያነሳሳ ነው፡፡

ባሕር ዳር ላይ የሚከናወኑ የቱሪዝም፣ የኢንዱስትሪ እና የግብርና ሥራዎች የነዋሪዎቿን ሕይወት ከማሻሻል አልፈው ሌሎችን እንዲስቡ ማድረግም ይገባል፡፡ “ሰው የምንስበውም፤ የምንገፋውም እኛው ነን፤ በአንድ ቀን የግልፍተኝነት እና የስሜት ጥፋት የከተማዋ ስም ሊበላሽ ይችላል፤ በትዕግስት፣ በጥበብ እና በማስተዋል ደግሞ በርካታ ጥበብ እና ሀብት ልንስብ እንችላለን” በማለት የከተማዋ ማኅበረሰብ ሥራ ወዳድ እና ሰላም ፈላጊ መሆናቸውን ሊያሳዩ እንደሚገባ መክረዋል፡፡ በተለይም በኢንዱስትሪ ፓርኩ ተቀጥረው የሚሠሩ ወጣቶች ሥራ መልመድ፣ በጨዋ ደንብ መንቀሳቀስ እና አሠሪዎችን ማክበር እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡

ዛሬ በተመረቀው ኢንዱስትሪ ፓርክ ብቻ ሳይታጠር ለቱሪዝም አማራጭ እንዲሆን በሚያስችል መልኩ መሥራት እንደሚያስፈልግም መክረዋል፡፡ ለመዝናኛ፣ ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የምርምር ቦታ እና ለቱሪዝም ምቹ በሚሆን መልኩ ከተማ አስተዳደሩ፣ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን እና የኢንዱስትሪ ፓርክ ተቋሙ በኃላፊነት ቢሠሩት ጥሩ እንደሚሆን መክረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት በባሕር ዳር ያለ እምቅ አቅምን ለቱሪዝም፣ ለኢንዱስትሪ እና ለውጪ ገበያ የሚመች ዘመናዊ ከተማ ለማድረግ ተፈጥሮ የሰጣትን ጸጋ በጭንቅላት ሥራዎች ማልማት ይገባል፡፡ ይህም ከምሥራቅ አፍሪካ ተመራጭ እንደሚያደርጋት ነው የገለጹት፡፡

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ፎቶ፡- ግርማ ተጫነ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleየበርሃ አንበጣ መፈልፈያ ቦታዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መከላከል ካልተቻለ ሥርጭቱ ወደ ሌሎች አካባቢዎችም ሊዛመት እንደሚችል የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡
Next articleየአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አራተኛ የወንጀል ችሎት የሰኔ 15 ጥቃት ምስክሮችን ከሰዓት በኋላ መስማት ይጀምራል፡፡