የበርሃ አንበጣ መፈልፈያ ቦታዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መከላከል ካልተቻለ ሥርጭቱ ወደ ሌሎች አካባቢዎችም ሊዛመት እንደሚችል የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡

152

ባሕር ዳር፡ መስከረም 27/2013ዓ.ም (አብመድ) የበርሃ አንበጣ መንጋው በስምንት ወረዳዎች በሚገኝ 85 ቀበሌዎች መከሰቱን ቢሮው ገልጧል፡፡

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ተስፋሁን መንግሥቴ በክልሉ ሰሜን እና ደቡብ ወሎ፣ ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር እና ሰሜን ሸዋ ዞኖች በስምንት ወረዳዎች በሚገኙ 85 ቀበሌዎች የበርሃ አንበጣ መንጋ መከሰቱን ገልጸዋል፡፡ ከ180 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ አሰሳ ተደርጎ ከ107 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የበርሃ አንበጣ መንጋው መኖሩ መታወቁን ምክትል ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

ችግሩ አሳሳቢ በሆነባቸው አካባቢዎችም በአንድ አውሮፕላን በቀን አምስት ጊዜ የኬሚካል ርጭት እየተደረገ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡ እስከዛሬ ድረስም ከ23 ሺህ 700 በላይ ሄክታር መሬት ላይ በአውሮፕላን የኬሚካል ርጭት ተደርጓል፤ ከ27 ሺህ 700 ሊትር በላይ ኬሚካልም ለርጭት ውሏል፡፡ የአካባቢውን ነዋሪዎች በማስተባበርም በባህላዊ መንገድ የመከላከል ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ አቶ ተስፋሁን ገልጸዋል፡፡

እስከዛሬ ከ65 ሺህ ሄክታር በላይ በበርሃ አንበጣ መንጋ የተወረረ መሬት በአውሮፕላን የኬሚካል ርጭት እና በባህላዊ መንገድ የመከላከል ሥራ መሠራቱን አቶ ተስፋሁን ተናግረዋል፡፡ የፌዴራል መንግሥትም የተሽከርካሪ፣ የአልባሳት፣ የመርጫ ማሣሪያ እና ሌሎች ድጋፎችን እያደረገ እንደሚገኝም ምክትል ኃላፊው ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጅ የመከላከል ሥራው እየተሠራ ቢገኝም የበርሃ አንበጣ መንጋው ከሚፈለፈልበት የአፋር ቆላማ አካባቢዎች ከመጀመሪያ ባለመሠራቱ እየተመለሰ እየገባ ማስቸገሩን ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

የአውሮፕላን ቁጥር በመጨመር ከምንጩ ጭምር ርጭት እንዲደረግም ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጋር መነጋገራቸውን አቶ ተስፋሁን ገልጸዋል፡፡ በዚህ ሦስት ቀናት ውስጥም አውሮፕላኖች እንደሚጨመሩ እና ርጭት እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡ አንበጣው በዚህ ወቅት በአንድ አንድ አካባቢዎች ከ20 እስከ 80 በመቶ በአንድ አንድ አካባቢዎች ደግሞ ሙሉ በሙሉ በሰብል እና በግጦሽ ቦታዎች ላይ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል፡፡ የበርሃ አንበጣ መፈልፈያ ቦታዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መከላከል ካልተቻለ ስርጭቱ ወደ ሌሎች አካባቢዎችም ሊዛመት እንደሚችል አቶ ተስፋሁን ገልጸዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሰራ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleማን ምን ይሥራ የሚለውን መለየት ብቻ ሳይሆን ሠርቶ እንደሚያሳይ የአማራ ኢኮኖሚ ሽግግር ማዕከል አስታወቀ፡፡
Next article“ሰው የምንስበውም፤ የምንገፋውም እኛው ነን…” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ